ቀጥታ፡

ባለፉት ሰባት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩት የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከ310 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2016(ኢዜአ)፦ ባለፉት ሰባት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩት የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከ310 ሚሊዬን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ገለጸ።

ማኅበሩ ለኢዜአ በላከው መረጃ፤ ባለፉት ሰባት ወራት ከ55 ሺህ ቶን በላይ የአበባ ምርት ወደ ውጭ ተልኮ ከ269 ነጥብ 7 ሚሊዬን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብሏል። 

በሌላ መልኩ በተመሳሳይ ወቅት ከ118 ሺህ ቶን በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ41 ሚሊዬን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱም ተጠቅሷል። 

በድምሩ በባለፉት ሰባት ወራት 310 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገልጿል። 

የተገኘው ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ24 ሚሊየን ዶላር ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቅሷል።

በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረ የፀጥታ ችግር ምክንያት ወደ ማዕከል የሚቀርበው የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች መቀነስ እንደ ምክንያት ተጠቅሷል። 

በተጨማሪም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የገበያ ዋጋ መዋዠቅና ከቀይ ባህር የፀጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የትራንስፖርት መስተጓጎል በዘርፉ የውጭ ገበያው ላይ ጫና ማሳደሩም ተመላክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም