ቀጥታ፡

ኢትዮ-ቴሌኮም ለ500 አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮ ቴሌኮም ለ500 የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የስምንት ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸው አጋዥ የአካል ድጋፍና የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን ድጋፍ አደረገ።

ተቋሙ ካደረገው ድጋፍ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ ለ199 አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የአካል ድጋፍና የቴክኖሎጂ መርጃ መሣሪያዎችን ዛሬ አስረክቧል። 

ድጋፉ 62 ዊልቸር፣ 25 ክራንች፣ ለአይነ ሥውራን የሚውል 59 ነጭ በትርና 53 የጆሮ አጋዥ ማዳመጫዎች አካቷል ተብሏል።

ቀሪ ድጋፎቹም በአገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች ለሚገኙ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በቀጣይ ጊዜያት የሚከፋፈል መሆኑም ተጠቅሷል።  

በኢትዮ-ቴሌኮም ዋና የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር መሣይ ውብሸት፤ ኢትዮ-ቴሌኮም አካታች የሆኑና ዘላቂነት ያላቸው ማኅበራዊ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህ ማዕቀፍ በዛሬው ዕለትም በትምህርት ዘርፉ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰው በቀጣይ ተቋሙ የሚያደርጋቸው ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። 


 

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው፤ ኢትዮ-ቴሌኮም ላደረገው ድጋፍ አመስግነው ድጋፉ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም