ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አምስት ተጨማሪ የአገር ውስጥ መዳረሻ ኤርፖርቶችን እየገነባ ነው - አቶ መስፍን ጣሰው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አምስት ተጨማሪ የአገር ውስጥ መዳረሻ ኤርፖርቶችን እየገነባ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ለማስፋት እየሰራ ነው። 

የሚያበራቸውን አውሮፕላኖች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ አየር መንገዱ 136  ዓለም አቀፍ እንዲሁም 22 የአገር ውስጥ መዳረሻዎች እንዳሉት ነው ያስረዱት።  

አየር መንገዱ ተጨማሪ የአገር ውስጥ መዳረሻዎችን ለማስፋት የያዘውን ዕቅድ ተከትሎ በአሁኑ ወቅት አምስት የአገር ውስጥ መዳረሻ ኤርፖርቶችን እየገነባ መሆኑን ተናግረዋል። 

ኤርፖርቶቹ የሚገነቡት ሚዛን ቴፒ አማን፣ ነጌሌ ቦረና፣ ያቤሎ፣ ጎሬ መቱና ደብረ ማርቆስ መሆናቸውን ገልጸው፤ አራቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ወደ ሥራ እንደሚገቡ ገልፀዋል። 

ይህም በአገር ውስጥ ያሉ ደንበኞች ፍላጎት ተከትሎ የሚተገበር ሲሆን፤ በቀጣይም ሌሎች መዳረሻዎችን ጥናት ላይ በተመሠረተ መልኩ ግንባታቸው የሚቀጥል ይሆናል ነው ያሉት። 

በሌላ በኩል ጉዳት የደረሰባቸው የአክሱምና የቀብሪደሃር ኤርፖርቶች እድሳት እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በቅርቡም ወደ ሥራ እንደሚገቡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

አየር መንገዱ በቀጣይም የአገር ውስጥ መዳረሻዎችን ለማስፋት በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊየን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ ነው።  

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም