በጎንደር ከተማ የወንዝ ዳርቻዎችና የተራራ ልማት ፕሮጀክት ለመጀመር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ የወንዝ ዳርቻዎችና የተራራ ልማት ፕሮጀክት ለመጀመር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ጎንደር ፤ መጋቢት 11/2016(ኢዜአ)፦ በጎንደር ከተማ በ21 ሚሊዮን ብር ወጪ የወንዝ ዳርቻዎችና የተራሮች ልማት የዲዛይን ስራን በማጠናቀቅ ወደ ተግባር ለመግባት እንቅስቃሴ መጀመሩን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡
የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ሱፐርቪዥን ቡድን የወንዝ ዳርቻና የተራራ ልማት የስራ ሂደት የደረሰበትን በተመለከተ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ እንደገለጹት፤ በከተማዋ የሚገኙ ወንዞችና ተራሮችን በማልማት ተጨማሪ የቱሪስት መስህብ በማድረግ የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም እየተሰራ ነው።
በዚህም 103 ሄክታር መሬት ላይ በሚገኙ ተራሮችና ወንዞች ላይ ጥናት በማካሄድ በ21 ሚሊዮን ብር በኢትዮጵያ ዲዛይንና ቁጥጥር ባለስልጣን አማካኝነት የዲዛይን ስራው እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የልማት ፕሮጀክቶቹ ለጉብኝትና ለሌሎች ስራዎች ወደ ከተማዋ ለሚመጡ ቱሪስቶችና እንግዶች "አማራጭ ተፈጥሮአዊ የመዝናኛና የማረፊያ ስፍራ ሆኖ እንዲያገለግል በዲዛይኑ ተካቶ እየተሰራ ነው" ብለዋል።
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ለእግረኞችና ለብስክሌት ተጓዦች የሚያገለግሉ መሰረተ ልማቶች የሚሟሉለት ሲሆን፤ የመዝናኛና የማረፊያ ስፍራዎችንም ያካተተ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የአዲስ አበባና የሌሎች የአገሪቷን ከተሞች መልካም ተሞክሮ በመቀመር እንደሚተገበር ጠቁመው፤ የዲዛይን ስራውን እስከ መጪው ሰኔ በማጠናቀቅም በቀጣዩ በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ የማልማት ሥራው እንደሚጀመር አስረድተዋል።
የወንዝ ዳርቻ ልማቱ ከተማውን አቋርጠው በሚፈሱት የአንገረብና ቀሃ ወንዞች ላይ እንደሚካሄድ ተገልጿል።።
ፕሮጀክቶቹ የከተማውን መዋቅራዊ ፕላን በጠበቀ መንገድ የሚሰሩ ናቸው ያሉት ደግሞ የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ የመሰረተ ልማት ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ታዘባቸው ነጋ ናቸው፡፡
የከተማውን ፈጣን የኢኮኖሚና የህዝብ እድገት ቁጥር ከግምት በማስገባት የመሰረተ ልማት ፍላጎትና የቴክኖሎጂ ተደራሽነትን ታሳቢ በማድረግ እንደሚከናወኑ ተናግረዋል፡፡
የሱፐርቪዥን ቡድኑ አባልና የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በበኩላቸው በኢትዮጵያ የከተሞች ታሪክ ረጅም እድሜና ገናና ስም ካላቸው ግንባር ቀደም ከተሞች ጎንደር አንዷ ነች ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ለአዳዲስ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች ትኩረት መስጠቱ የጎንደርን ዘመን ተሻጋሪ የኪነጥበብ፣ የባህልና የኪነ ህንፃ መገኛ ስፍራ መሆኗን አጉልቶ እንደሚያሳይ አመልክተዋል።
በተጨማሪም የወንዝ ዳርቻና የተራራ ልማት ፕሮጀክቶቹ ቱሪስቶች ከጉብኝት መልስ የሚያርፉበትና የሚዝናኑበት አማራጭ መዳረሻ ሆነው በሚያገለግሉ መልኩ ሊገነቡ ይገባል ብለዋል።
በፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ የተመራው የሱፐርቪዥን ቡድን በጎንደር ቆይታው በከተማው የሚካሄዱ የመሰረተ ልማት፣ የኢንቨስትመንትና የሌማት ትሩፋት ፕሮጀክቶችን ጎብኝቷል፡፡