በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ደንብ የተቋሙን አቅም ለማጎልበት ያስችላል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2016(ኢዜአ)፦በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት አዲስ ደንብ የተቋሙን ገቢ በማሳደግ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማስፋትና ለማጠናከር እንደሚያስችል ተገለጸ። 

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 16/2016 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ኢንስቲትዩቱ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚከፈሉ የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ ደንብ በሙሉ ድምፅ መፅደቁ ይታወሳል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንድማገኝ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለኢንስቲትዩቱ ለደረጃዎች ምልክት ይከፈል የነበረው ዋጋ አነስተኛ ነበር።  

ይህንንም ተከትሎ ተቋሙ በአገልግሎቱ ማግኘት የሚገባውን ገቢ ማጣቱን ተናግረዋል።

አምራቾችም የደረጃዎች ምልክትን በዝቅተኛ ዋጋ ስለሚገዙት ተገቢውን ዋጋ ያለመስጠት ችግሮች እንደሚስተዋልባቸው ነው የገለጹት። 

በመሆኑም በሚኒስትሮች ምክር ቤቱ የፀደቀው አዲሱ ደንብ ለአገልግሎት የሚከፈሉ ክፍያዎች ከፍ ለማድረግ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።  

ተቋሙ የሚሰበስበውን ገቢ ማሳደግ ከተቻለ፤ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማስፋትና ለማጠናከር እንደሚያስችል ገልፀዋል። 

አምራቾች በጥራት እንዲያምኑና ደረጃውን የጠበቀ ምርት የማምረት ባህል ለማስረጽ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።      

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት በአገሪቱ ብቸኛው ደረጃ የማውጣት ኃላፊነት ያለው ተቋም ነው።

ኢንስቲትዩቱ በዓለም አቀፍ የጥራት ተቋም (አይ ኤስ ኦ)፣ዓለም አቀፍ ኤሌክትሮቴክኒክ ኮሚሽን(አይ ኢ ሲ) እና የአፍሪካ የደረጃዎች ድርጅት (አርሶ) በደረጃዎች ላይ ተሳትፎ የሚያደርግ ብቸኛው የጥራት መሠረተ- ልማት ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም