በሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች የሚገኙ የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች የሚገኙ የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆኑ
ሰቆጣ፤ መጋቢት 10/2016(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል በሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች የገጠር ቀበሌዎች የሚኖሩ 7 ሺህ ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን በክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የወልዲያ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃብታሙ ማኛው ለኢዜአ እንደገለጹት የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ የሆኑት በሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች በሚገኙ የሶስት ቀበሌዎች ነዋሪዎች ናቸው።
የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች በበኩላቸው የኤሌክትሪክ አገልግሎት መግባቱ ሕይወታቸውን በተሻለ መንገድ ለመምራት እንዳገዛቸው ተናግረዋል።
ጽህፈት ቤቱ በተያዘው በጀት ዓመት በተመደበለት ከ62 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በዞኖቹ አምስት ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀዋል።
በዚህም ባለፉት ሰባት ወራት ባደረገው እንቅስቃሴ በዋግ ኽምራ የደብል ማርያምና ቤላ እንዲሁም በሰሜን ወሎ ቆባ ቀበሌዎች ነዋሪዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
ቀበሌዎቹን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግም 55 ኪሎ ሜትር የመካከለኛና ዝቅተኛ ኃይል ተሸካሚ መሥመር መዘርጋቱንና ሥራውን ለማከናወንም ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አስታውቀዋል።
በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራትም በሰሜን ወሎ ዞን በመቄት ወረዳ መስፍና ቀበሌንና በራያ ቆቦ ወረዳ አዩብህ ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በአካባቢው ጉዳት ደርሶበት የነበረውን ከሰቆጣ -ፃታ- እጥቅኑ 54 ኪሎ ሜትር የምሰሶ ተከላና መስመር ዝርጋታ በተያዘው ሣምንት እንደሚጀመር አቶ ሃብታሙ ተናግረዋል።
በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የደብል ማርያም ቀበሌ ሊቀመንበር ቄስ አሰፋ መሰለ በቀበሌያቸው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ስላልነበር ሲቸገሩ እንደነበር ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት መጀመሩ እናቶች እህል በእጅ ከመፍጨትና ተማሪዎች በኩራዝ ከማጥናት ያወጣቸው ሲሆን፣ በደን ላይ የሚደርሰውን ጭፍጨፋ ለመቀነስ እንደሚያስችል አመልክተዋል።
የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ወንድሙ ማሞ ''የኤሌክትሪክ አገልግሎት በማግኘታችን የተሻለ ሕይወት ለመምራት አግዞናል'' ብለዋል።