ኢትዮጵያ በስደተኞች አያያዝ እና ጥበቃ በአርዓያነት ተጠቃሽ ሀገር ነች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በስደተኞች አያያዝ እና ጥበቃ በአርዓያነት ተጠቃሽ ሀገር ነች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በስደተኞች አያያዝ እና ጥበቃ በአርዓያነት የምትጠቀስ ሀገር ናት ሲሉ የአሜሪካ የስደተኞች እና የፍልሰት ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ጁልዬታ ቫልስ ኖይስ ተናገሩ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የአሜሪካ የስደተኞች እና የፍልሰት ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር ጁልዬታ ቫልስ ኖይስን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በትምህርት፣ በስደተኞች፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በአለም አቀፍ መድረክ በትብብር እየሰራች መሆኑን አስረድተዋል።
ስደተኞችን አስመልክቶም መንግስት በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ከ 1ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን በማስተናገድ የቤት፣ የምግብ እና የመጠለያ አቅርቦት በማሟላት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በውይይቱ ላይ የአሜሪካ የስደተኞች እና የፍልሰት ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ጁልዬታ ቫልስ ኖይስ እንዳሉት ኢትዮጵያ ብዙ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች ተቀብላ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት የምታከናውነው ተግባር በአርአያነት የሚጠቀስ ነው።
ረዳት ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ በስደተኞች አያያዝ እና ጥበቃ በአርዓያነት የምትጠቀስ ሀገር ናት ሲሉም ገልጸዋል።
የአሜሪካ መንግስትም ይህን ስራ በመደገፍ አብሮ እንደሚሰራ ረዳት ሚኒስትሯ ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።