በሂሳብ አያያዝና ኦዲት ላይ የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት እየተመዘገበባቸው ነው- ዶክተር እዮብ ተካልኝ - ኢዜአ አማርኛ
በሂሳብ አያያዝና ኦዲት ላይ የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት እየተመዘገበባቸው ነው- ዶክተር እዮብ ተካልኝ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2016(ኢዜአ)፦በሂሳብ አያያዝና ኦዲት ላይ የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ከፓን አፍሪካ የአካውንታንቶች ፌደሬሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት አውደ-ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እና የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ሊቀመንበር ዶክተር እዮብ ተካልኝ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ መድረኩ በሂሳብ አያያዝና በኦዲት የሥራ ሂደት ያሉ የጥራት ችግሮችን ማስተካከል ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።
የሂሳብ አያያዝና ኦዲት የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እንዲሁም የኢንቨስትመንት የደም ሥር መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘርፉ የተጠናከረ የትብብር ሥራ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በዘርፉ ያሉ ሥራዎችን በማስተካከል ረገድ በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልፀዋል።
የአይ ኤፍ አር ኤስ ትግበራ እና የመንግሥት የፋይናንስ ሥርዓት ማስተካከያዎችን ለአብነት ጠቅሰው፤ ተቋማት የፋይናንስ ሪፖርታቸውን በቦርዱ አጽድቀው የሚያቀርቡበት አሠራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል።
በሂሳብ አያያዝና ኦዲት ላይ የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የተጠናከረ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያም ሥራ ላይ ሊውል የሚችለው የተደራጀና እውነተኛ የፋይናንስ ሪፖርት ሲኖር ብቻ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተርና የቦርዱ አባል መሠረት ዳምጤ፤ በሂሳብ አያያዝና ኦዲት ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች በሙያው ላይ ያለውን እምነትና መተማመን እየሸረሸረ መምጣቱን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በመስከረም ወር የተቀበለችው የዓለም አቀፍ የሕዝብ አገልግሎት ዘርፍ አካውንቲንግ ደረጃ "IPSAS" የፋይናንስ ግልፀኝነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት በጋራ መሥራት እንደሚገባ ገልጸው፤ ጥራት ያለው የኦዲት አገልግሎት በመስጠት ለሀገር ኢኮኖሚ ብልፅግናን ማበርከት የሚችል አቅም መገንባት ይገባል ብለዋል።
የፓን አፍሪካ የአካውንታንቶች ፌዴሬሽን የጥራት አማካሪ ቡድን ሊቀመንበር ጆርጅ ሞኩአ፤ ፌዴሬሽኑ አህጉራዊ መፍትሔዎችን በማልማት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የጥራት ፎረም በመመስረት የጥራት ደረጃዎችን እየመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ባለሙያዎች ድንበር ተሻግረው እንዲሰሩ የተያዘውን ትልም እውን የሚያደርግ መሆኑን አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ሂክመት አብደላ፤ በመድረኩ የአህጉሪቱ የዘርፉ ባለሙያዎች የጋራ ግንዛቤ ይዘው በትብብር እንዲሰሩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉበት ያለው አውደ- ጥናት ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ አራት ቀናት የሚካሄድ ይሆናል።