ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ስዊዘርላንድ በመሰረተ ልማት ግንባታ ጥብቅ ታሪካዊ ቁርኝት አላቸው - አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና ስዊዘርላንድ በመሰረተ ልማት ግንባታ ጥብቅ ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ቁርኝት እንዳላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ተናገሩ።

የስዊዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢግናዚዮ ካሲስ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በአዲስ አበባ የስዊዘርላንድ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ የአዲስ ሕንፃ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል። 


 

በመርኃ ግብሩ የሀገራቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎችና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል፡፡

አዲሱ ሕንፃ የአምባሳደር መኖሪያ ቤትና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ክፍሎች እንደሚኖሩት በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

በሥነ-ስርዓቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ፤ ኢትዮጵያ እና ስዊዘርላንድ ጠንካራ የሆነና ታሪካዊ  የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ስዊዘርላንድ በታሪክ፣ በኪነ-ሕንፃ፣ በፈጠራ፣ በባቡር፣ በውሃ፣ ቴሌኮም እና ፖስታ አገልግሎት መሰረተ ልማት ግንባታ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ቁርኝት እንዳላቸው አስታውሰዋል።

በአዲስ አበባ የስዊዘርላንድ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ የሚገነባው ሕንፃ ከሀገራቱ ባለፈ ቀጣናዊ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብርን ለማሳደግ መሰረት እንደሚሆን ገልጸዋል። 

ስዊዘርላንዳዊው አልፍሬድ ኤልግ በኢትዮጵያ የቤተ-መንግሥት፣ ባቡር፣ ድልድይና የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ እጃቸው እንደነበረበት አስታውሰዋል፡፡

የኤምባሲው የኪነ-ሕንፃ ግንባታ ዲዛይን ከሸሆጀሌ ቤተ-መንግሥት ቅርጽ መወሰዱ በራሱ ትናንትን ዛሬ ላይ የሚያሳይ ድንቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

የስዊዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢግናዚዮ ካሲስ፤ የሕንፃ ግንባታው በጠንካራ መሰረት ላይ የቆመውን የሁለቱን አገራት ዲፕሎማሲዊ ወዳጅነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።


 

ግንባታው የአገራቱን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ከማሳደግ ባለፈ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነታችንን ለማጠናከር ቁርጠኞች መሆናችንን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የስዊዘርላንድ አምባሳደር ታማራ ሞናን፤ በፕሮጀክት ግንባታ እንቅስቃሴው አስተዋጽኦ ላደረጉ የኪነ-ሕንፃ፣ የህግ እና ሌሎች ሙያተኞች ምስጋና አቅርበዋል።


 

ፕሮጀክቱ የአፍሪካዊያን የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባን ዕውቅና የሚያሳድግ ነው ብለዋል።

ከትላንት ጀምሮ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የስዊዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢግናዚዮ ካሲስ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ጋር በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸው ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም