ሰሞኑን ከሲስተም ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ችግር እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ደንበኞችን ሊያጭበረብሩ የሚሞክሩ መኖራቸውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ሰሞኑን ከሲስተም ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ችግር እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ደንበኞችን ሊያጭበረብሩ የሚሞክሩ መኖራቸውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰሞኑን ከሲስተም ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ችግር እንደ አጋጣሚ ለመጠቀም የሚሞክሩ አጭበርባሪዎች በመኖራቸው ደንበኞቹ ራሳቸውን እንዲጠብቁ አስጠነቀቀ።
እነዚህ አጭበርባሪዎች በአብዛኛው ከባንክ የደወሉ በማስመሰል “የተዘጋ ሂሳባችሁን እንክፈትላችሁ”፣ “ሂሳባችሁ እንዳይዘጋ የምንልክላቹሁን ኮድ አስገቡ” የሚል የማጭበርበሪያ ዘዴ በመጠቀም የዘረፋ ሙከራ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ባንኩ እንደደረሰበት ገልጿል።
ሆኖም ባንኩ ስልክ ደውሎ ስለ ደንበኞች የሂሳብ መረጃ የሚጠይቅበት፣ ሂሳብ የሚከፍትበትም ሆነ የሚዘጋበት አሰራር እንዲሁም ደንበኞች እንዲጠቀሙበት የሚልከው ምንም አይነት ኮድ እንደሌለ አስታውቋል።
ባንኩ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ ማንኛውም የባንኩ ደንበኛ መሰል ሁኔታ ሲገጥመው ምንም ዓይነት እርምጃ ከመውሰድ በመቆጠብ፤ በአቅራቢያ ወደሚገኝ ቅርንጫፍ በመሄድ አሊያም በ951 ለባንኩ የደንበኞች ጥሪ ማዕከል በመደወል ስለሁኔታው መረጃ መጠየቅ እንዳለበትም አስገንዝቧል።