የአድዋ ድል መታሰቢያ የአድዋን ታሪክ በቅጡ ለማወቅ ከማገዙ በዘለለ የሕዝብ ኅብረትና ትብብር ጠቀሜታን ያስተምራል - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል መታሰቢያ የአድዋን ታሪክ በቅጡ ለማወቅ ከማገዙ በዘለለ የሕዝብ ኅብረትና ትብብር ጠቀሜታን ያስተምራል
አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 10/2016(ኢዜአ)፦ የአድዋ ድል መታሰቢያ የአድዋን ታሪክ ለማወቅ ከማገዙ በዘለለ አገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሕዝብ ኅብረት አስፈላጊነት እንደሚያስተምር የእስልምና ኃይማኖት መምህራንና አባቶች ተናገሩ።
ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የመጡ የእስልምና ኃይማኖት መምህራንና የእምነቱ አባቶች የአድዋ ድል መታሰቢያን ዛሬ ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ በኢትዮጵያ ትልቅ የታሪክ ኃብት ስለሆነው አድዋ ድል ያላቸውን መረጃ ሊያጎለብቱላቸው የሚችሉ መረጃዎችን ማግኘት እንደቻሉ የእስልምና ኃይማኖት አባቶቹ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼይኸ አብዱላዚዝ አብዱልዋሊ፤ የአድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያዊያንን ማንነት የሚገልጽ ጥልቅ የአገር ኃብት ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
መታሰቢያው ኢትዮጵያዊያን በኅብረት የአገሪቱን ሕልውና ለማስጠበቅ የከፈሉትን ዋጋ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያዊያን እርስ በእርስ ያለንን አንድነት ማጠናከር እንዳለብን ትምህርት ይሰጣልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የፕሬዝዳንቱ ልዩ አማካሪና የኃይማኖት መምህር ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በበኩላቸው መታሰቢያው የቀደሙ አባቶች የአገሪቱን የግዛት አንድነት ለመጠበቅ የከፈሉትን ዋጋ ይዘክራል ብለዋል።
ይህም በአንድነት ከቆምንና ተባብረን ከሠራን አገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ እንደሚቻል ትምህርት ለመውሰድ የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ብዙ ሊነገሩና መታሰቢያ ሊቆምላቸው የሚገቡ የትልቅ ታሪክ ባለቤት ናት ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ኡስታዝ መሐመድ አባተ ናቸው።
መታሰቢያው አድዋ ሲነሳ ሊታወቅ የሚገባውን መረጃ ያገኙበት መሆኑን ጠቅሰው የአገሪቱን ታሪካዊ ኃብቶች የሚያሳዩ ሌሎች መታሰቢያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ሊሰፉ እንደሚገባም ገልጸዋል።