ቀጥታ፡

በደቡብ ኦሞ ዞን ፈጣንና ፍትሐዊ የጤና ልማትን ለማረጋገጥ በቅንጅት የተሰራው ሥራ ውጤት እየተመዘገበበት ነው

 ሀዋሳ ፤ መጋቢት 10/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኦሞ ዞን አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮች አካባቢዎች ፈጣንና ፍትሐዊ የጤና ልማትን ለማረጋገጥ በቅንጅት የተሰራው ሥራ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤትና የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ገለጹ።

''የተጠናከረ የጤና ሥርዓት ለፈጣንና ፍትሐዊ የእናቶችና ሕፃናት ጤና ልማት!” በሚል መሪ ሀሳብ በደቡብ ኦሞ ዞን ዲመካ ከተማ የመንግስትና የማህበረሰብ አካላት የጋራ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤትና የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ፋውንዴሽኑ በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮች አካባቢ ፍትሐዊ የጤና ልማትን ለማረጋገጥ እየሰራ ነው።

በነዚህ አካባቢዎች ፈጣንና ፍትሐዊ የጤና ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ከሆኑ ባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት በመስራቱ በተለይ በእናቶችና ሕፃናት የጤና አገልግሎት ላይ ለውጥ መመዝገቡን አስታውቀዋል።

ለአብነት በሀመር ወረዳና አካባቢው ከሁለት ዓመት በፊት 34 በመቶ የነበረው በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች የሚወልዱ እናቶች መጠን በአሁን ወቅት ወደ 52 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።

ፋውንዴሽኑ በዘርፉ ዕድገት እንዲመዘገብ በወረዳዎች ለሚገኙ መንግሥታዊ አካላት፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የጎሳ መሪዎች፣ የልምድ አዋላጆችና ሌሎች አካላት የክህሎት ማዳበሪያ ሥልጠና መስጠቱን ተናግረዋል።

እንዲሁም አምቡላንሶችን፣ ሞተር ብስክሌቶችንና የአልትራ ሳውንድ መሣሪያዎችን ድጋፍ ማድረጉን ነው ወይዘሮ ሮማን  የገለጹት።

በተለይም በጤና ተቋማት የመውለድ መጠንን ከፍ ለማድረግ ከመንግሥታዊ አካላት፣ ከጎሳ መሪዎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር የሚሰራው ሥራ እንደሚያጠናክር አስታውቀዋል።


 

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አቅናው ካውዛ በበኩላቸው የጤና አገልግሎት ፍትሐዊነትና ጥራትን ማረጋገጥ በ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ ውስጥ ከተቀመጡ ግቦች መካተቱን  አስረድተዋል።

በተለይ በደቡብ ዞሞ ዞን በአርብቶ አደሮች አካባቢ በቅንጅት በተሰሩ ሥራዎች በእናቶች የወሊድ አገልግሎት፣ በክትባት፣ በቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ላይ ተስፋ ሰጪ ለውጥ መመዝገቡን አስታውቀዋል።


 

የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታምራት አሰፋ በበኩላቸው በዞኑ 32 ጤና ጣቢያዎች፣ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልና 172 የጤና ኬላዎች ለህብረተሰቡ የጤና አገልግሎት በመስጠት ላይ  መሆናቸውን ተናግረዋል።

''ፋውንዴሽኑ በተለይ የእናቶችንና ሕጻናትን ጤና ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው'' ያሉት አቶ ታምራት፤ በሥልጠና፣ በአምቡላንስና በህክምና መሳሪያዎች እያደረገ ያለው ድጋፍ ለጤና አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል እገዛው የላቀ መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ ሃላፊው ገለጻ ፋውንዴሽኑ ለወላድ እናቶች ማቆያና የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በማሟላትና በሌሎች ተግባራት እያደረገ ባለው ድጋፍ  የዞኑ ጤና ዘርፍ እመርታ እንዲያመጣ አድርጓል።

ፋውንዴሽኑን ጨምሮ ባለድርሻዎች ባደረጉት ርብርብ በዞኑ ከ10 ዓመታት በፊት ሰባት በመቶ የነበረው በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች መጠን አሁን ላይ ወደ 80 በመቶ ከፍ ማለቱን ኃላፊው አስታውቀዋል።


 

በሀመር ወረዳ የሲምበሌ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ሲልቦ አልጎ ከዚህ በፊት በጤና ተቋማት መውለድ ባለው ጥቅም ላይ የነበረው የህብረተሰቡ ግንዛቤ ማነስና በቂ የጤና ተቋማት አለመኖር ወላድ እናቶችና ሕጻናት ለሞት ይጋለጡ ነበር።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱ እናቶች የመውለጃ ቀናቸው ሲቃረብ ወደ ጤና ተቋማት በመውሰድና በዚያው ቆይተው እንዲወልዱ በማድረግ እፎይታ አግኝተናል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የፌዴራል፣ የክልል እንዲሁም የዞንና ወረዳ አስተዳደር የመንግሥት አመራር አባላት፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የጎሳና የአካባቢ አስተዳደሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም ተሳትፈዋል ።  

የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን በደቡብ ኦሞ ከጤና ዘርፍ በተጨማሪ በአካባቢ ጥበቃ፣ በኢኮ ቱሪዝም፣ የሴቶችንና የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጎልበት እየሰራ መሆኑ ተመላክቷል።

በግብርና ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮች ሕይወት ላይ ለውጥ ለማምጣት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም