በዞኑ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ደብረ ብርሃን፣መጋቢት 10 /2016 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሰላምን በዘላቂነት በማረጋገጥ የጽንፈኛውን ቡድን ሴራ ለማምከን እየተከነወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖሰት አስታወቀ።
ኮማንድ ፖስቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት የተከናወኑ የሰላም ማስፈንና የጸጥታ ተግባራትን በደብረ ብርሃን እየገመገመ ነው።
የኮማንዶና አየር ወለድ አዛዥና የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብዴታ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ኮማንድ ፖስቱ የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የጽንፈኛውን ቡድን ሴራ ለማምከን በትኩረት እየሰራ ነው።
የመከላከያ ሰራዊት ከሌሎች የፌዴራልና የክልል የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመተባበር በተከናወኑ የጸጥታ ማስከበር ተግባራት ሰላምን ማስፈን መቻሉን ተናግረዋል።
የዛሬው መድረክ ዓላማም በኮማንድ ፖስት አባላት እስካሁን የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም የተመዘገቡ ተጨባጭ ለውጦችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ክፍተቶችን በማረም ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የተገኘውን ሰላም ወደ ዘላቂ በማሸጋገር አካባቢውን ለልማትና መልካም አስተዳደር የተመቸ የሚያደርጉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን አስረድተዋል።
በግምገማው መድረክ በአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አህመዲን መሀመድን ጨምሮ ከደብረ ብርሃን ከተማ እና ከሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።