ቀጥታ፡

የደብረ ብርሃን ከተማ የመሬት አስተዳደር የካዳስተር ምዝገባ ስራው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እያስገኘ ነው - ነዋሪዎች 

ደብረብርሃን፣መጋቢት 10/ 2016 (ኢዜአ)፡-በደብረ ብርሃን የከተማ መሬት አያያዝ ሥርዓትን በካዳስተር ቴክኖሎጂ በማዘመን የሚነሱ የሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለመፍታት የተሰራው ስራ አበረታች መሆኑን  የከተማው ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

እድሜ ጠገብ የሆነችው ደብረ ብርሃን የኢንዱስትሪና ኢንቨትስመንት ማዕከል የመሆኗን ያህል በዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ረገድ በርካታ ሊከናወኑ የሚገቧቸው ተግባራት አሏት።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከተማ አስተዳደሩ የመሬት አስተዳደርን ለማዘመን የሚረዱ የካዳስተር ምዝገባ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ነው።

በዚህ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት የካዳስተር ምዝገባ ስራው መሠራቱ የከተማዋን የመሬት ሀብት በአግባቡ ለአገልግሎት ለማዋል የጎላ ድርሻ አለው።

ከከተማው  ነዋሪዎች  መካከል  መምህር መርሻ ስማቸው እንደገለጹት ቀደም ሲል የነበረው የከተማው  የመሬት አስተዳደር ስርዓት ባረጀው የወረቀት አያያዝ መሆኑ ለአጭበርባሪዎችና ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ አድርጎት ቆይቷል፡፡

በዚህም በሐሰተኛ ማስረጃ ካርታ ማሰራት፣ የመንግስት መሬትን በህገ ወጥ መውረር፣ ከይዞታ ውጪ የሆኑ ቦታዎችን አካቶ መያዝና ሌሎች ችግሮች ይስተዋሉ እንደነበር በማሳያነት አንስተዋል፡፡

አሁን የከተማ አስተዳደሩ ካዳስተርን በመተግበር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የከተማ ቦታን መመዝገብና መረጃውን መያዝ መጀመሩ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን እየፈታ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ዓለማየሁ ጨርቆስ በበኩላቸው አዲሱ የይዞታ ማረጋገጫ ምዝገባ በቴክኖሎጂ ታግዞ መካሄዱ  ነዋሪዎች ሀብታቸውን  በአግባቡ ለመጠቀምና ለማስተዳደር  የሚያስችል ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊት ማዘጋጃ ቤት በመሄድ ዜጎች አገልግሎት ሲፈልጉ "ፋይል  ጠፋ፣ ተበላሸ"  በማለት ጉዳዩ በከንቲባ ኮሚቴ ተይቶ እስኪወሰን ከሁለት እስከ ሰባት ዓመት ይጓተት እንደነበር ጠቁመው፤ አዲሱ አሰራር ይሄን ችግር የሚፈታ ነው ብለዋል፡፡

የካዳስተር አሰራር መጀመሩ ያለ አግባብ  የተያዙ የመንግስት መሬቶችን ለህዝባዊ ልማት እና ጥቅም ለማዋል የሚያስችል ነው" ያሉት ደግሞ ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ብርቱካን ገደቡ ናቸው።

የከተማ አስተዳደሩ መሬት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ እታለማሁ ይምታቱ እንደገለጹት የካዳስተር ምዝገባው አሠራር ዜጎች በህግ አግባብ ያፈሩትን ሀብት  በነፃነት ለመጠቀም የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ 

ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ  እስካሁን በተሰራው የከተማው የካዳስተር ምዝገባ ስራ በሶሰት ክፍለ ከተሞች በ56 ሰፈሮች የሚገኙ ይዞታዎችን በካዳሳተር ስርዓት መረጃቸው እንዲያዝ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ወርቃለማሁ ኮሰትሬ በበኩላቸው የካዳስተርና የዲጅታላይዜሽን ስራው መካሄዱ ከተማዋን ለኢንቨስትመንት፣ ለኑሮና ቱሪዝም ልማት ተመራጭ እንድትሆን ያደርጋል ብለዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በያዝነው ዓመት ከ39ሺህ 500  በላይ ባለ ይዞታዎችንና የመንግስት ቦታዎችን ወደ ዲጅታላይዜሽን ሲስተም የማስገባት ስራ መሰራቱን አስረድተዋል፡፡

ይህም ያለአግባብ የተያዙ የመንግስትና የህዝብ ሀብቶችን በመለየት የመሬት አስተዳደር ስርዓቱን ግልጽነት ተጠያቂነትና ውጤታማነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም