ቀጥታ፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለኢኮኖሚ ጥቅም ለማዋል የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ---ዶክተር ፍጹም አሰፋ

ሚዛን አማን፣መጋቢት 10/2016(ኢዜአ)፡-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያሉትን የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ ለኢኮኖሚ ጥቅም ለማዋል በፌዴራልና በክልሉ መንግስት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ።

በሚኒስትሯ የሚመራው የፌዴራል የሱፐርቪዥን ቡድን በክልሉ የድጋፍና ክትትል ሥራ እያከናወነ ነው።


 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በክልሉ ቤንች ሸኮ ዞን የልማት ሥራዎችን በጎበኙበት ወቅት ለኢዜአ እንዳሉት፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብዙ የተፈጥሮ ሀብቶች አሉ።

"እነዚህን የተፈጥሮ ሀብቶች አልምቶ ለተሻለ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማዋል በፌዴራልና በክልሉ መንግስት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ" ብለዋል።

ለግብርና ሥራ ምቹ ከሆነው የመሬት፣ የውሃና የደን ሀብት በተጨማሪ በክልሉ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ አልምቶ መጠቀም እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሯ እንዳሉት በክልሉ አርሶ አደሩ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ ልማት እያለማ ያለበት ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ሀብቱን አልምቶ ለመጠቀም እያደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ ሆኖ ኢኮኖሚውን መደገፍ እንዲችል በአካባቢው መሠረተ ልማትን ማሟላት ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

በዋናነት አርሶ አደሮቹ ምርቶቻቸውን ወደገበያ ለማውጣት እየገጠማቸው ያለውን የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር ለመፍታት በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

በፌዴራል መንገዶች የሚሰሩ ነባር የመንገድ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ማስጀመር ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት ዶክተር ፍጹም አስገንዝበዋል።

ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎች ለገጠሩ የህብረተሰብ ክፍል እንዲደርሱ በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር በትኩረት እንደሚሰራም ዶክተር ፍጹም አመልክተዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካብትን በበኩላቸው ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ችግር በአካባቢው መኖሩን አስታውሰው፣ በዞኑና በኅብረተሰብ አቅም መፈታት ያለበትን እየፈታን እንሄዳለን ብለዋል።

በዞኑ ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው የኤክስፖርት ምርቶች እንዳሉበት ጠቁመው፣ የፌዴራል መንግስት የጀመረውን የድጋፍና ክትትል ሥራ እንዲሁም የመንገድ መሠረተ ልማቶችን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

በክልሉ ከቤንች ሸኮ ዞን ብቻ በየዓመቱ ከ100 ሺህ ቶን በላይ ቡና እንደሚሰበሰብ የገለጹት ደግሞ የዞኑ ግብርና፣ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ ናቸው። 

በተጨማሪም በቆሎ፣ ሩዝ፣ ማሾ፣ ሰሊጥ እንዲሁም ኮረሪማ፣ ቁንዶ በርበሬ፣ ጥምዝ፣ እርድ፣ ዝንጅብልና መሰል የቅመማ ቅመም ምርቶች በስፋት እንደሚመረቱ ገልጸዋል።

በዞኑ ደቡብ ቤንች ወረዳ የቦተርሳይት ቀበሌ አርሶ አደር ይስሐቅ ሐረፋ በቆሎ፣ ቡናና ሌሎች የግብርና ምርቶችን በማምረት እንደሚተዳደሩ ተናግረዋል።


 

በአካባቢው የተሽከርካሪ መንገድ ባለመሠራቱ ምክንያት ከቤት ፍጆታ የሚተርፈውን የግብርና ምርት ለገበያ አውጥቶ ለመሸጥ እንቸገራለን ብለዋል።

ሌላው የጌሊት ቀበሌ አርሶ አደር ሙሳ ሰይፉ በበኩላቸው በመንገድ ችግር ምክንያት ለግብርና ምርታቸው የተሻለ ዋጋ አግኝተው ተጠቃሚ እየሆኑ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

"የመንገድ ችግሩ አቅሙ እያለ ከዚህ በተሻለ አምርተን ተጠቃሚ እንዳንሆን በማድረጉ አሁን ላይ ምርታችን ከቀለብ እያለፈ አይደለም" ያሉት አርሶ አደሩ፣ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የመንገድ ችግራቸውን እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም