በአቶ መላኩ አለበል የተመራ የፌዴራል አመራሮች የክትትልና ድጋፍ ቡድን በአፋር ብሄራዊ ክልል ምልከታ አካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በአቶ መላኩ አለበል የተመራ የፌዴራል አመራሮች የክትትልና ድጋፍ ቡድን በአፋር ብሄራዊ ክልል ምልከታ አካሄደ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 10/2016(ኢዜአ)፦በኢፌዴሪ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የተመራ የፌዴራል አመራሮች የክትትልና ድጋፍ ቡድን በአፋር ብሄራዊ ክልል ምልከታውን አካሒዷል።
የክትትልና ድጋፍ ቡድኑ ከመጋቢት 06/2016 ዓ.ም ጀምሮ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባና ከክልሉ ካቢኔ አባላት ጋር ባካሄደው የጋራ ውይይት የተጀመረ ሲሆን ባለፉት ጊዜያት በክልሉ ዞን-1 የተከናወኑ ዋና ዋና የልማት እንቅስቃሴዎች ምልከታ ተደርጓል።
በተለይም የበጋ መስኖ ልማት እንቅስቃሴ(የበቆሎ፣ የስንዴ፣ የጓሮ አትክልት...ወዘተ)፣ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራሞች አፈፃፀም(የአሳ ልማት፣ የዶሮና ወተት ልማት)፣ የማንፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ (የጨው ማምረት) እንዲሁም የትምህርት፣ ጤና እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን የሚመለከቱ አጠቃላይ የልማት ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው ምልከታ ተደርጎባቸዋል።
በተጨማሪም በዞኑ የስራ እድል ፈጠራን በሚመለከት የተከናወኑ ስራዎች በድጋፍ ቡድኑ የታዩ ሲሆን ወጣት ሴቶች በእደ ጥበብ ስራ፣ ወጣቶች በእርሻ የግብርና ስራ፣ በአሳ ልማት፣ በጨው ማምረት እና በሌሎችም ዘርፎች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን በተካሄደው የመስክ ምልከታ ማረጋገጥ ተችሏል።
ሌሎችም የአረንጓዴ አሻራ፣ የከተማ ውበትና ፅዳት እንዲሁም የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥና የመንግስት ገቢ የድጋፋዊ ሱፐርቪዥኑ አካል የነበሩ ሲሆን በዞኑ የተካሄደው ድጋፋዊ ሱፐርቪዥን በትላንትናው እለት ተጠናቅቋል።
በማጠቃለያው ላይ የዞኑና ምልከታ የተደረገባቸው ወረዳዎች አመራሮች የተገኙ ሲሆን የድጋፍ ቡድኑ ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል በዞኑ አጠቃላይ የልማት ስራ ላይ የተስተዋሉ ጥንካሬዎችንና በቀጣይ ደግሞ ትኩረት የሚደረግባቸውን ጉዳዮች በዝርዝር ግብረ-መልስ ሰጥተዋል።
በየደረጃው ያለው አመራርም የህብረተሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስና የተጀመረውን የልማት እንቅስቃሴ የበለጠ ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አሳስበዋል።