ቀጥታ፡

በክልሎቹ ከ480 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ አርሶ አደሩ ጋር መድረሱ ተገለጸ

ሆሳዕና/ቦንጋ መጋቢት 10/2016 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ከ480 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ አርሶ አደር ጋር መድረሱን የክልሎቹ ግብርና ቢሮዎች ገለጹ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር፣ ከማዳበሪያ አቅርቦት ጋር ሲነሳ የነበረውን ችግር ለመቅረፍ ክልሉ በልዩ ትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

ለዚህም ለ2016/17 የምርት ዘመን ከ800 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን ጠቅሰው ከዚህ ውስጥ ከ420 ሺህ ኩንታል በላይ ለአርሶ አደሩ ማዳረስ መቻሉን ገልጸዋል።

ማዳበሪያው በክልሉ በሚገኙ በ10 ዩኒየኖችና በ462 የህብረት ስራ ማህበራት በኩል እየተሰራጨ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀድያ ዞን ሌሞ ወረዳ ቦብቾ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዳዊት ኤርዳፖ፣ ባለፈው ዓመት ከአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ እጥረት አጋጥሟቸው እንደነበረ አስታውሰዋል።

ዘንድሮ የአፈር ማዳበሪያ ወቅቱን ጠብቆ መቅረብ በመቻሉ ገዝተው የግብርና ስራቸውን እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

በተያያዘም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ አስራት አሰፋ፣  የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የክልሉ የዚህ ዓመት የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት 194 ሺህ 768 ኩንታል ሲሆን ከዚህ ውስጥ እስካሁን 165 ሺህ 335 ኩንታል ወደ ክልሉ እንደገባና 60 ሺህ 19 ኩንታሉ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ጠቁመዋል።

አሁንም ተጨማሪ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ እየገባ መሆኑን የገለፁት አቶ አስራት፣ በመጠንም ሆነ በወቅቱ ከማቅረብ አንፃር የጎላ ችግር አለመኖሩንም ተናግረዋል።

ከምርጥ ዘር ፍላጎት አንጻር 58 ሺህ 703 ኩንታል ለማሰራጨት ታቅዶ እስካሁን 37 ሺህ 484 ኩንታል ማሰራጨት የተቻለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት የአርሶ አደሩን ምርጥ ዘር ፍላጎት በራስ የማሟላት ግብ ይዞ ውጤታማ ስራ እያከናወነ መሆኑን ደግሞ የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ እምሩ ወዬሳ ገልጸዋል።

ድርጅቱ በክልሉ ላሉ አርሶ እና አርብቶ አደሮች ለተለያየ አየር ጠባይ ተስማሚ የሆኑ የሰብል እና የመኖ ምርጥ ዘሮችን በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ስራ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

ድርጅቱ በሙከራ ደረጃ ከ13 ሄክታር በላይ መሬት ላይ ማሾና ቦሎቄ በማምረት ያገኘውን ምርት ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት መቻሉን አቶ እምሩ ገልፀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም