በየአካባቢው የሚገኙ ፀጋዎችን አሟጦ በመጠቀም ልማትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል -ዶክተር አለሙ ስሜ - ኢዜአ አማርኛ
በየአካባቢው የሚገኙ ፀጋዎችን አሟጦ በመጠቀም ልማትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል -ዶክተር አለሙ ስሜ

ሆሳዕና ፤መጋቢት 9/2016 (ኢዜአ)፦ በየአካባቢው የሚገኙ ፀጋዎችን አሟጦ በመጠቀም ልማትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር አለሙ ስሜ ገለጹ።
በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ የተመራ የፌዴራል የድጋፍና ክትትል ቡድን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀላባ ዞን ቁሊቶ ከተማ የተለያዩ የልማት ስራዎች ጎብኝቷል።
ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በየአካባቢው የሚገኙና ያልተነኩ የልማት ጸጋዎችንና አቅሞችን በአግባቡ በመጠቀም የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ ።
በክልሉ የሀላባን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች የተጀመሩ የልማት ስራዎችና የለውጥ እንቅስቃሴዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰው አሁንም የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በዛሬው ዕለት የተመለከቱት የሀላባና አጎራባች ዞኖች ሰላም ለመጠበቅና ለማረጋገጥ እየተሰራ የሚገኘው ስራ ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን ጠቅሰው የተጀመሩ የልማት ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማደግ እንዳለበትም አክለዋል።
በአርሶ አደሩ የሚመርቱ ምርቶችን በህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት በማቅረብ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ ስለመሆኑም በመስክ ጉብኝታቸው ማረጋገጥ መቻላቸውን አብራርተዋል።
የቁሊቶ ከተማን ውብና ማራኪ በማድረግ ረገድ አመራሩ ከማህበረሰቡ ጋር በቅርበት መስራት እንዳለበትም አመልክተዋል።
የሀላባ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀጂ ኑርዬ በበኩላቸው በዞኑ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሌማት ትሩፋትና በሌሎች ዘርፎች እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እየተመዘገበባቸው ይገኛል ብለዋል።
በእንስሳት ልማት 106 የተሻሻሉ የእንሰሳት ዝርያዎችን በማምጣት በወተትና በእንሰሳት ተዋጽኦ ልማት አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ጉብኝቱም በዞኑ እየተከናወኑ የሚገኙ የተለያየ ስራዎችን ጠንካራና ደካማ ጎን በመለየት ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዞኑ በሁሉም ዘርፍ ያሉ ሀብቶችን በአግባቡ በመጠቀም የነዋሪውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
በመስክ ምልከታ መርሐ ግብሩ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን በነገው እለት በከንባታ ዞን የተለያየ አካባቢዎች የመስክ ምልከታ እንደሚደረግም ተገልጿል።