በመዲናዋ በሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ላይ ለሚካሄደው የሪፎርም ትግበራ ውጤታማነት አመራሩ በትጋት መስራት ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ በሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ላይ ለሚካሄደው የሪፎርም ትግበራ ውጤታማነት አመራሩ በትጋት መስራት ይጠበቅበታል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2016(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ በ16 የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ላይ ለሚካሄደው ሪፎርም ትግበራ ውጤታማነት አመራሩ በትጋት መስራት እንዳለበት የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው በ16 ተቋማት ላይ የሪፎርም ስራ የዝግጅት ምዕራፍን በማጠናቀቅ ወደ ትግበራ መሸጋገሩን አስታውቋል፡፡
የቢሮው ኃላፊ ጣሰው ገብሬ(ዶ/ር ) ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለፁት በተቋማት የአሰራር ስርዓት ለውጥ በማስፈለጉና ብቃት ያለው የሰው ኃይል አደረጃጀትና ተጠያቂነትን ለማስፈን በ2016 በጀት ዓመት በ16 ተቋማት ላይ የሪፎርም ስራ ሲሰራ ቆይቷል።
ሪፎርሙን ተከትሎ የአሰራር ስርዓት ማሻሻያ የማድረግና በሶስተኛ ወገን የሚሰሩ አገልግሎቶችንና ተቋማትን የመለየት ስራ ተከናውኗል ብለዋል።
በቴክኖሎጂ የሚደገፉ አገልግሎቶች መለየታቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት መገንባት የሚያስችሉ 42 ፕሮጀክቶች እንደሚተገበሩ አብራርተዋል።
የሰራተኛ ብቃት ምዘና በገለልተኛ ተቋማት መሰጠቱንም በመግለጫቸው አንስተዋል።
የብቃት ምዘናው ከ19ሺህ በላይ የሆኑ ሰራተኞች መውሰዳቸውን ጠቅሰው ከተፈታኞቹ መካከል 33 ነጥብ 3 በመቶ አመራሮች እንዲሁም 50 ነጥብ 6 በመቶ ሠራተኞች ማለፋቸውን ተናግረዋል።
ምዘናውን ካለፉት መካከል 99 በመቶ የሚሆኑ ኃላፊዎች፣ 88 በመቶ የቡድን መሪና ሰራተኞች መመደባቸውን ጠቁመው ፈተናውን ያላለፉትም በድልድል ደንቡ መሰረት ሁለት ደረጃ ዝቅ ብለው መመደባቸውን ገልጸዋል።
ምዘናውን ተከትሎ ከ17 ሺህ በላይ ሰራተኞች በሁለት ዙር የአቅም ግንባታ ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
የሪፎርሙ የዝግጅት ምዕራፍ ተጠናቆ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ትግበራ መግባቱን ገልፀው እንደዝግጅት ምዕራፉ ሁሉ ለትግበራ ምዕራፉ ውጤታማነት በተለይ የተቋማት አመራሮች በትጋት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።