ቀጥታ፡

በደቡብ ወሎ ዞን በበጋ መስኖ ስንዴና በሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብር የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ናቸው - ዶክተር ለገሰ ቱሉ

ደሴ ፤ መጋቢት 9/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ወሎ ዞን በበጋ መስኖ ስንዴና በሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብር የተከናወኑ ተግባራት በአካባቢው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ መሆናቸውን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለፁ።

በዶክተር ለገሰ ቱሉ የተመራ የፌደራል መንግስት የድጋፍና ክትትል ቡድን በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ዙሪያና ተሁለደሬ ወረዳዎች የበጋ ወቅት ስራዎችና የሌማት ቱርፋት ተግባራትን ተመልክቷል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት ኢኮኖሚውን በማነቃቃት ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በደቡብ ወሎም የበጋ መስኖ ስንዴን የማልማትና በሌማት ትሩፋትም አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በማምረት ለህብረተሰቡ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

የስራ እድል ፈጠራውን ከሌማት ቱርፋት ጋር በማስተሳሰር በወተት፣ በእንቁላል፣ በማርና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች በማምረት የገበያ ክፍተቱን ለመሙላት እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች ነው ብለዋል።


 

ይህም የተቀረጸው የአገር በቀል ኢኮኖሚ ውጤታማነት ማረጋገጫ መሆኑን በዞኑ እየተከናወነ ያለው ስራ ማሳያ መሆኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

የፌዴራል መንግሥትም በየጊዜው የድጋፍ ቡድን በመላክ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው ድጋፉ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።


 

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን በበኩላቸው በዞኑ በበጋ መስኖ ስንዴ ከለማው 26 ሺህ ሄክታር መሬት ከ700 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።

በሌማት ቱርፋት መርሃ ግብርም ሁሉም የዞኑ ነዋሪ በአካባቢው አትክልትና ፍራፍሬ፣ ዶሮና የመሳሰሉትን በማልማትና በማርባት በንቃት እንዲሳተፍ መደረጉን ገልጸዋል።


 

በዶሮ እርባታ በተፈጠረልን የስራ እድል ለመለወጥ እየሰራን ነው ያለችው ደግሞ በደሴ ዙሪያ ወረዳ የ015 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ሀቢባ ኢብራሂም ናት።

ዘንድሮ 61 ሆነው በመደራጀት 1 ሺህ 100 እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን ማርባት መጀመራቸውን ጠቁማ በቀን ከ600 በላይ እንቁላል ማግኘት መጀመራቸውን ጠቁማለች።

የፌደራል መንግስት የድጋፍ ቡድኑ በሐይቅ ከተማ በገበታ ለትውልድ የሚለማውን የሎጎ ሐይቅንም ጎብኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም