በመዲናዋ የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የሪፎርም ስራ ይከናወናል- ጃንጥራር አባይ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2016(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የሪፎርም ስራ እንደሚከናወን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር  አባይ ገለጹ። 

የመዲናዋ የሕብረት ሥራ ኮሚሽን "የማኅበራትን ኃብትና ንብረት ከብክነት በመጠበቅ የአባላቱንና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነትን እናረጋግጥ"በሚል መሪ ኃሳብ ሲያካሒድ የነበረውን መርሃ ግብር አጠናቋል።

በመርሃ ግብሩ ማጠናቀቂያ ላይ የከተማ አስተዳዳሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣የክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች የህብረት ስራ ማህበራት ተወካዮች ተገኝተው በሪፎርሙ ላይ ውይይት አድርገዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ፤ሕብረት ስራ ማሕበራት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸው ሪፎርም እየተዘጋጀ  ነው።

ሪፎርሙ የማኅበራቱን የአሠራር ሥርዓት የሚያዘምን እንዲሁም ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር የቁጥጥርና የክትትል ሥራን ለማጠናከር የሚያስችል እንደሆነ ነው የጠቆሙት።  

በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራትና የአሠራር ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ  ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝም ነው ያብራሩት።

በአሁኑ ወቅት ከተማ አስተዳደሩ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አሠራራቸውን በማሻሻል ምርቶችን በስፋት ወደ ገበያ እንዲያቀርቡ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል ።

በማህበራቱ ላይ ጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ልዕልት ግደይ በበኩላቸው፤ኮሚሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የህብረት ስራ ማህበራትና ተገልጋዩን ያካተተ ጥናት በማካሔድ የሪፎርም ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።


 

ሪፎርሙ የተዘጋጀበት ዋና ዓላማ ጠንካራ ተቋም በመገንባት ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል  ነው ብለዋል።

ሪፎርሙን ለመተግበርም ከህብረት ስራ ማህበራትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የተለያዩ ተግባራትን እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ ውስጥም በዘርፉ ስራ ላይ የሚውል ቴክኖሎጂን የማበልፀግና አሳሪ የሆኑ መመሪያዎችን የማሻሻል ስራም አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።

የየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ አራት የሸማች ሕብረት ስራ ማህበራት አመራር ኮሚቴ ሰብሳቢ ዳኘ ከበደ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የቱሉ ዲምቱ ሸማቾች  ማህበር ስራ አሲኪያጅ ወይዘሮ  ሰሀራ ንጉሴ፤ ሪፎርሙ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራርን በመተግበር የማህበራቱ አሰራር ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስተካከል እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

በመዲናዋ ከ9 ሺህ 800 በላይ ህብረት ስራ ማህበራት እንደሚገኙ የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም