የኢትዮጵያ የሸማቾች መብት ጥበቃ ማህበራት ጥምረት ተመሰረተ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የሸማቾች መብት ጥበቃ ማህበራት ጥምረት ተመሰረተ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2016(ኢዜአ)፦ በሸማቾች መብት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራ የኢትዮጵያ የሸማቾች መብት ጥበቃ ማህበራት ጥምረት ተመስርቷል፡፡
ጥምረቱ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴዔታ አቶ እንዳለው መኮንን፣ የንግዱ ዘርፍ ባለድርሻ አካለትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተማ ተመስርቷል፡፡
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴዔታ አቶ እንዳለው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ሸማቾች በግብይት ስርዓቱ ላይ ትልቁን ድርሻ ይዘው ቢገኙም መብቶቻቸው ግን እየተከበረ አይደለም፡፡
በከፈሉት ዋጋ ልክ ደህንነቱ እና ጥራቱ የተጠበቀ ተመጣጣኝ ምርትና አገልግሎት አያገኙም ነው ያሉት፡፡
ይህ ደግሞ የራሳቸውን አደረጃጀት ፈጥረው ለመብቶቻቸው በጋራ መታገል ባለመቻላቸው የመጣ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ሽማቾች መንግስት በአዋጅ ያስቀመጠላቸውን መብት በአግባቡ ለመጠቀም መደራጀት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ለዚህም ሚኒስቴሩ በቀጥታ የሸማቾች መብት እንዲከበር ከሚሰራቸው ስራዎች ጎን ለጎን ጠንካራ አደረጃጀት እንዲፈጥሩ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አመላክተዋል፡፡
በዚህም በዛሬው እለት ክልሎችንና ሁለቱን ከተማ አስተዳደሮች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮጵያ የሸማቾች መብት ጥበቃ ማህበራት ጥምረት እንዲመሰረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ዛሬ የተመሰረተው ጥምረት በአገር አቀፍ ደረጃ ሸማቾች በህግ የተሰጣቸውን መብት እንዲያውቁ እና በግብይት ሒደት የሚያጋጥማቸውን የመብት ጥሰቶች በጋራ እንዲታገሉ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጥምረቱ ይህን ለማድረግ ከፍተኛ ሃላፊነት የተጣለበት መሆኑን በመገንዘብ ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ጥምረቱ የሚያከናውናቸው ተግባራት እውን እንዲሆኑ ከጎኑ እንደሚቆም አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሸማቾች መብት ጥበቃ ማህበራት ጥምረት በፕሬዝዳንት እንዲመሩ የተመረጡት እንግዳ አስፋው በበኩላቸው፣ የሸማቾች መብት በአዋጅ ያለ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ግን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ አለመደረጉን ገልጸዋል፡፡
ይህም ሸማቾች ስለመብቶቻቸው በቂ ግንዛቤ ባለመያዛቸውና መብቶቻቸው ሲጣሱም ከለላ የሚሆንላቸው ማህበራት ባለማቋቋማቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዛሬ የተመሰረተው ጥምረት በተለይ ሽማቹን ስለመብቱ ግንዛቤ የመፍጠርና መብቶች ተጥሰው ሲገኙም ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን የህግ ከለላ እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በዛሬው እለት ዓለም አቀፍ የሸማቾች ቀንን "በህብር መብታችንን እናስከብር" በሚል መሪ ሃሳብ አክብሯል።