በግብርና ፣በትምህርት ፣በጤናና በሌሎች ዘርፎች የተገኙ ውጤቶች የሚበረታቱ ናቸው - ኢንጂነር አይሻ መሀመድ - ኢዜአ አማርኛ
በግብርና ፣በትምህርት ፣በጤናና በሌሎች ዘርፎች የተገኙ ውጤቶች የሚበረታቱ ናቸው - ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 9/2016(ኢዜአ)፦በግብርና ፣በትምህርት ፣በጤና እና በሌሎች ዘርፎች የተሰሩት ስራዎች የሚበረታቱና ሊሰፉም እንደሚገባ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ገለጹ።
በኢንጂነር አይሻ መሃመድ የተመራ የፌደራል የድጋፍ እና ክትትል ቡድን በአሶሳ ዞን ባምባሲ ወረዳና በባምባሲ ከተማ አስተዳደር የመስክ ልማት ስራዎችን ጎብኝቷል።
በጉብኝቱም ሚኒስትሯና የክትትል ቡድኑ የበጋ መስኖ ስንዴ ፣የዶሮ እርባታ ፣ አፈርና ውሃ እቀባ ስራዎችና በሌሎች ዘርፎች የተከናወኑት የልማት ስራዎችን መመልከት ችለዋል፡፡
በዚህ ጊዜም ኢንጂነር አይሻ በግብርና ፣በትምህርት ፣በጤና እና በሌሎች ዘርፎች የተሰሩትን ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸው በቀጣይ በሁሉም አካባቢ ሊሰፉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ወረዳውና የከተማ አስተዳደሩ በአካባቢው የሚገኙ ጸጋና ምቹ ሁኔታዎችን ተጠቅሞ ከዚህ በላይ ማልማት እንደሚኖርበትም ገልጸዋል።
የክትትልና ሱፐርቪዥን ቡድኑ አባላት በመስክ ምልከታው በሁሉም ዘርፍ የታዩት የልማት ስራዎች በተዋረድ ያለው የመንግስትና የፓርቲው ክትትልና ቅንጅታዊ የስራ ውጤት መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ክፍተቶችን በማረም በሁሉም ዘርፍ የበለጠ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አብራርተዋል።
በመስክ ምልከታው የፌዴራል የሱፐርቪዥን ቡድንን ጨምሮ ፣የክልል ፣የዞን እና የወረዳው አመራሮች መሳተፋቸውን ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።