ከፍተኛ የጸኃይ ጨረር በሰው ጤና ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል በሚል በማኅበራዊ ሚዲያው የሚሰራጨው መረጃ ኃሰተኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከፍተኛ የጸኃይ ጨረር በሰው ጤና ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል በሚል በማኅበራዊ ሚዲያው የሚሰራጨው መረጃ ኃሰተኛ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2016(ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ ከፍተኛ የጸኃይ ጨረር በሰው ጤና ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል በሚል ማኅበራዊ ሚዲያው የሚሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ሰሞኑን በማኅበራዊ ትስስር ገፆች በአዲስ አበባ በጤና ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ከፍተኛ የፀኃይ ጨረር እንደሚኖር ተደጋጋሚ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።
ይህን ተከትሎም አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ጉዳት ያደርስባቸዋል በሚል ከመማሪያ ክፍላቸው እንዳይወጡ ክልከላ ማድረጋቸውን ኢዜአ ከተለያዩ ምንጮች ማረጋገጥ ችሏል።
አንዳንድ ወላጆችና የከተማዋ ነዋሪዎችም በዚሁ መረጃ ምክንያት መደናገር እንደተፈጠረባቸውም እንዲሁ።
ጉዳዩን አስመልክቶ ኢዜአ የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የስፔስና ፕላኔተሪ ሳይንስ ሥራ ክፍል መሪና ተመራማሪ ንጉሴ መዝገበ (ዶ/ር)ን አነጋግሯል።
ባለሙያው፤ ከፍተኛ የጸኃይ ጨረር በሰው ጤና ላይ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል በሚል በማኅበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው መረጃ ኃሰተኛና ከሳይንሱ ውጪ ነው ብለዋል።
የጸኃይ ጨረር በሰዎች ጤና ላይ ሊያስከትል የሚችለው የጤና ጉዳት አለመኖሩንም አረጋግጠዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን ከጸኃይ የሚነሱ ሞገዶች ወይም ቅንጣቶች ወደ መሬት ወርደው ሰዎች ላይ ጉዳት የማድረስ አቅም የላቸውም ነው ያሉት።
ይልቁንም ከጸኃይ የሚነሱ ጨረሮች በብዛት የሚያጠቁት ስፔስ ላይ ያሉ ሳተላይቶችን የመገናኛና የኮሙኑኬሽን መሣሪያዎችን መሆኑንም አብራርተዋል።
አለም ዓቀፍ የስፔስ ትንበያዎች እንዲህ አይነት ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ምንም አይነት ፍንጭ አለመስጠታቸውንና የተናፈሰው ሐሰተኛ መረጃ ምንጩ የማይታወቅ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ የሚሰራጩ መረጃዎችን ትክክለኛነት ከሚመለከታቸው አካላት ማጣራት እንዳለበት ገልጸው፣ የእለት ተእለት እንቅስቃሴውን ያለምንም ሥጋት ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል።