በባንኩ የደንበኞች የግል አካውንት ላይ የደረሰ ምንም አይነት ጉዳት የለም - የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ - ኢዜአ አማርኛ
በባንኩ የደንበኞች የግል አካውንት ላይ የደረሰ ምንም አይነት ጉዳት የለም - የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2016(ኢዜአ)፡- በባንኩ የደንበኞች የግል አካውንት ላይ የደረሰ ምንም አይነት ጉዳት አለመኖሩን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ።
ባንኩ ሰሞኑን አጋጥሞት የነበረውን የአገልግሎት መቋረጥ ችግር አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
በዚህም በባንኩ የደንበኞች የግል አካውንት ላይ የደረሰ ምንም አይነት ጉዳት የለም ሲሉ የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በመግለጫቸው ይፋ አድርገዋል።
ባንኩ የውስጥ አሰራሩን ለማዘመን ሲያደርግ በነበረው እንቅስቃሴ አርብ መጋቢት 6 ለሊቱን በተፈጠረ ስህተት ምክንያት ጤናማ ያልሆነ የገንዘብ እንቅስቃሴ እንደነበረ መጠቆማቸውን የኢቢሲ ዘገባ ያመላክታል።
ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው እንደገለጹት የተፈጠረው ክስተት ከሳይበር ጥቃት ጋር የተያያዘ አይደለም።
አርብ ለሊት ብቻ ከ490 ሺህ በላይ የገንዘብ ልውውጥ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን ይህ የገንዘብ ልውውጥ ጤናማ የሆነውንም እንደሚጨምር ተጠቁሟል።
ገንዘብ በተለያየ መንገድ ጤናማ ባልሆነ መልኩ ከባንኩ በማውጣት ላይ በዋናነት የተሳተፉት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ አብዛኛው ተማሪዎች በባንኩ በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት የወሰዱትን ገንዘብ እየመለሱ መሆኑ ገልፀዋል።
የባንኩን ጥሪ ተቀብለው ገንዘቡን ተመላሽ ላደረጉ ተማሪዎች ባንኩ ምንም አይነት ክስ እንደማይመሰርትም ማስታወቃቸውን በዘገባው ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተደጋጋሚ በሀገራት በሚደገፉ ትልልቅ ተቋማት ጭምር የሳይበር ጥቃቶች ሙከራዎች ቢያጋጥሙትም አስተማማኝ የሳይበር ደህንነት ያለው ተቋም በመሆኑ ሁሉንም ሲያከሽፍ እንደቆየ ነው ፕሬዝዳንቱ የገለፁት።
የደረሰው ጉዳት ከባንኩ አጠቃላይ ሀብት አንፃር በጣም አነስተኛ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ የደንበኞች የግል አካውንት ላይ የደረሰ ምንም አይነት ጉዳት ባለመኖሩ ደንበኞች ምንም አይነት ስጋት ሊገባቸው እንደማይገባ የባንኩ ፕሬዝዳንት መግለጻቸውም ተጠቁሟል።