ቀጥታ፡

በዘንድሮ ዓመት የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን ለመውሰድ ከ670 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተመዝግበዋል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2016(ኢዜአ)፦በዘንድሮ ዓመት የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን ለመውሰድ ከ670 ሺህ በላይ የተማሪዎች ምዝገባ መካሄዱን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ገለጸ። 

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለዘንድሮው አገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተሳካ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው። 

ይህንንም ተከትሎ ተማሪዎች የሚፈተኗቸውን የትምህርት ዓይነቶች አውቀው ዝግጅት እንዲያደርጉ  ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መከናወኑን አንስተዋል።

ተማሪዎች በሥነ-ልቦና እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል።

ለአገር አቀፉ የ12ኛ ክፍል ፈተና የሚቀመጡ የተፈታኝ ተማሪዎች ምዝገባ ከየካቲት 3 እስከ የካቲት 30/2016 ዓ.ም እንደሚያከናውን ተቋሙ መግለጹ ይታወሳል። 

ይህንንም ተከትሎ ተቋሙ የፀጥታ ችግር ካለባቸው አንዳንድ አካባቢዎች በስተቀር በአብዛኛው አገሪቱ አካባቢዎች የተማሪዎች ምዝገባ ተካሂዶ መጠናቀቁን ጠቁመዋል። 

በዚህም እስካሁን ከ670 ሺህ በላይ ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ መመዝገባቸውን ገልፀዋል።

የተቀሩት የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተፈታኝ ተማሪዎች ምዝገባ ደግሞ በዚህ ሣምንት እንደሚከናወን ነው ያረጋገጡት።    

የፈተና ዝግጅት ሥራው የአገሪቱን ሥርዓተ ትምህርት የተከተለና ተማሪዎቹን በአግባቡ ለመመዘን በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል። 

የፈተናው ዝግጅት እየተገባደደ መሆኑን አንስተው በቀጣይ የፈተናው ሕትመት እንደሚጀመር ገልፀዋል። 

የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና የመስጫ ሰሌዳ ወደፊት ይፋ ይሆናል ተብሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም