የአየር መንገዱን የደንበኞች አገልግሎት ይበልጥ ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የአየር መንገዱን የደንበኞች አገልግሎት ይበልጥ ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2016(ኢዜአ)፦ የአየር መንገዱን የደንበኞች አገልግሎት ይበልጥ ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፤ በአየር መንገዱ እየተከናወኑ ያሉ በርከት ያሉ ስራዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በተያዘው በጀት ዓመት በስድስት አዳዲስ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ለመብረር አቅዶ እስካሁን ሶስቱን ማሳካቱን ጠቅሰዋል።
በአውሮፕላን ግዥም ስምንት አውሮፕላኖችን ለመግዛት ታቅዶ እስካሁን የስድስት አውሮፕላን ግዥ መሳካቱን ገልጸዋል።
በቀጣይነትም የ124 አውሮፕላኖች የግዥ ትእዛዝ መኖሩን ጠቁመዋል።
ከመሰረተ ልማት አንፃርም የኢ-ኮሜርስ ፋሲሊቲ፣ የሃይል አቅርቦት ሰብስቴሽን እንዲሁም የሀገር ውስጥ በረራ ተርሚናል ግንባታ ተጠናቆ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
በግንባታው ዘርፍ የተርሚናል ሁለት ማስፋፊያ መደረጉን አንስተው አሁን ላይ ተጨማሪ የማስፋፊያ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከደንበኞች አገልግሎት ጋር በተያያዘ በተመዘገበው ስኬት አየር መንገዱ የተለያዩ አለም አቀፍ እውቅና እና ሽልማቶችን ማግኘቱንም ጠቅሰዋል።
በአገልግሎት አሰጣጡ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮች ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለዋል።
የአየር መንገዱን የደንበኞች አገልግሎት ይበልጥ ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
አየር መንገዱ ለደንበኞች አገልግሎት ሁሉንም ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸው ቅሬታዎች ሲኖሩ የሚስተናገዱበት ስርዓት መዘርጋቱን አንስተዋል፡፡
የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ተከትሎ ተገቢውን ምርመራ በማድረግ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አንስተዋል፡፡
የአየር መንገዱን የደንበኞች አገልግሎት ይበልጥ ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የተናገሩት፡፡
በቀጣይም በቢሾፍቱ ከተማ በዓመት 100 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚያስችልና 300 አውሮፕላኖችን የሚያቆም አዲስ ሚጋ አውሮፕላን ማረፊያ እንደሚገነባም ጠቁመዋል፡፡
ይህም አሁን ያለውን ተርሚናል በአራት እጥፍ የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።