ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ስዊዘርላንድ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በተለያዩ የትብብር መስኮች ለማጠናከር ይሰራሉ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2016(ኢዜአ)፦ለበርካታ ዓመታት የቆየውን ኢትዮጵያንና የስዊዘርላንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰሩ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ገለጹ። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ካሉት ከስዊዘርላንድ አቻቸው ኢግናዚዮ ካሲስ ጋር በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እንዲሁም በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ተወያይተዋል። 

የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያና ስዊዘርላንድ ግንኙነታቸውን በተለያዩ የትብብር መስኮች ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።   

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ሁለቱ ሀገራት ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው አገራት ናቸው ብለዋል። 

በርካታ የስዊዘርላንድ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት መሰማራታቸውን ጠቁመው ይህንን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል። 

በሁለቱ ሀገራት መካከል ከዚህ ቀደም የተደረሱ የትብብር ሥምምነቶች ተግባራዊ ለማድረግም እንዲሁ። 

በሌላ በኩል በፕሪቶሪያው የሠላም ሥምምነት፣ በሽግግር ፍትህና ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአፈፃጸም ሂደት ላይ አጽንኦት ሰጥተው መምከራቸውንም አንስተዋል። 

የስዊዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢግናዚዮ ካሲስ በበኩላቸው፤ የሀገራቱን የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ተስማምተናል ነው ያሉት። 

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ልማት፣ ሰላምና ደኅንነት ወሳኝ ሚና የምትጫወት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል። 

ስዊዘርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በፍልሰት ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል። 

የሥራ ጉብኝታቸውም የስዊዘርላንድና ኢትዮጵያን የቆየ ታሪካዊ ወዳጅነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ዓላማ ያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም