ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የቆጣሪ ውል እድሳቱን እስከ ሰኔ 30/2016 ዓ.ም አራዘመ 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚያገለግል የቆጣሪ ውል የእድሳት ጊዜ እስከ ሰኔ 30/2016 ዓ.ም ማራዘሙን ገለጸ።

ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ተጠያቂነትን ለማስፈን ያስችላል ያለውን ይኸው የውል እድሳት ከሕዳር 1 እስከ መጋቢት 30/2016 ዓ.ም ነበር ለማከናወን አቅዶ ወደ ሥራ የገባው።

ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች የቆጣሪ ውል እድሳቱን እስከ ሰኔ 30/2016 ዓ.ም መራዘም ማስፈለጉን ነው የተቋሙ የኮርፖሬት የኮሙኑኬሽን ዳይሬክተር መላኩ ታዩ ለኢዜአ የገለጹት።  

የውል እድሳቱ ቆጣሪ ከወሰዱ ከአምስት ዓመታት በላይ የሆናቸውን ደንበኞችን ብቻ የሚመለከት መሆኑን ተናግረው እድሳቱ ምንም አይነት ክፍያ እንደማይጠይቅ ጠቁመዋል። 

በመሆኑም ደንበኞች በአቅራቢያቸው ባሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ማዕከል በመሄድ በተሰጠው የጊዜ ገደብ የውል እድሳቱን እንዲያከናውኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።    

ከሕዳር 1/2016 ጀምሮ ከ21 ሺ በላይ ደንበኞች የውል እድሳት ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገልጿል። 

የውል እድሳቱ ቆጣሪን ለማይታወቅ አካል የሚያስተላልፉ ደንበኞችን ለመቆጣጠር፣ የኃይል ሥርቆትን ለማስቀረት እንዲሁም  የኃይል መቆራረጥ ችግር ለማቃለል እንደሚያስችል ተገልጿል። 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም