ቀጥታ፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራት የአሠራር ሥርዓታቸውን በማሻሻል ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመረው ሪፎርም ሊጠናከር ይገባል  

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2016(ኢዜአ)፦ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የአሠራር ሥርዓታቸውን በማሻሻል የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የጀመረው  የሪፎርም ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ገለፁ።

የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን "የማኅበራትን ኃብትና ንብረት ከብክነት በመጠበቅ የአባላቱንና የኅብረተሰብ ተጠቃሚነትን እናረጋግጥ" በሚል መሪ ኃሳብ ሲያካሂድ የቆየው ንቅናቄ ማጠቃለያ መርኃ ግብር እየተካሄደ ነው። 

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ በዚሁ ጊዜ  እንደገለጹት፤ በመዲናዋ የኅብረት ሥራ ማኅበራት እየተስተዋሉ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የሪፎርም ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ሪፎርሙ የማኅበራቱን የአሠራር ሥርዓት የሚያዘምን እንዲሁም ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር የቁጥጥርና የክትትል ሥራ ለመሥራት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።  

ይህም ብቻ ሳይሆን በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራትና የአሠራር ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ  ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝም ነው ያብራሩት።

ከተማ አስተዳደሩ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አሠራራቸውን በማሻሻል ምርቶችን በስፋት ወደ ገበያ እንዲያቀርቡ ለማስቻል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም ኮሚሽኑ የጀመረው የሪፎርም ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት።  

በመድረኩ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የሁሉም ክፍለ ከተማና ወረዳ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተወካዮች ተገኝተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም