ቀጥታ፡

በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ግዳጃቸውን በአኩሪ ገድል በመፈፀም ረገድ የሴቶች ሠራዊት አባላት ሚና እየጨመረ ነው

ድሬዳዋ ፤ መጋቢት 9/2016(ኢዜአ)፦ በተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ግዳጃቸውን በአኩሪ ገድል በመፈፀም ረገድ የሴቶች ሠራዊት አባላት ሚና እየጨመረ መሆኑን ብርጋዴር ጄኔራል ሁሉአገርሽ ድረስ ተናገሩ።

ብርጋዴር ጄኔራል ሁሉአገርሽ ይህን የተናገሩት ሁርሶ ኮንቲንጀንት ትምህርት ቤት ለሰላም ማስከበር ተግባር የሰለጠኑ የሠራዊት አባላት ባስመረቀበት ስነስርዓት ላይ ነው።


 

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ብርጋዴር ጄኔራል ሁሉአገርሽ ድረስ በዘመቻው ለሚሳተፉት ተመራቂ ሴት የሠራዊቱ አባላት ተሞክሯቸውን በማካፈል የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ አበረታትተዋል።

ብርጋዴር ጄኔራል ሁሉአገርሽ በዚሁ ወቅት ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ሴቶች የአገር መከላከያ ሠራዊትን ተቀላቅለው የአገራችንን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ እያደረጉት የሚገኘው ተሳትፎና ውጤታማነት እየጨመረ ይገኛል።

ከዚህ ጎን ለጎን በተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አገራችን ያላትን ከፍታና ተመራጭነት በማሳደግ ረገድም አበርክቷቸው እየጎለበተ መምጣቱን በመግለፅ።

ወደ ደቡብ ሱዳን ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ የተዘጋጁት ሴት የሠራዊት አባላትና አመራሮች ቁጥር ከምንጊዜውም በላይ ከፍ ማለቱን ለአብነት አንስተዋል።

ይህም ሴቶች በአፍሪካ በተለይም በምስራቅ አፍሪካ አገሮችና ህዝቦች መካከል ትስስር በመፍጠርና አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን እየፈፀሙ የሚገኙት ጀብድና ተቀባይነት እያደገ መምጣቱን ያመላክታል ብለዋል።

በቀጣይም አገርን በአምባሳደርነት ወክለው ለሰላም ማስከበር በሚጓዙበት አካባቢዎች ህዝባዊ ባህሪያትን በመላበስ አገራዊና ተቋማዊ ግዳጆችን በብቃት በመወጣት የኢትዮጵያን ገፅታ ያሳድጋሉ ብለዋል።

ለሰላም ማስከበር ዘመቻ ዝግጁ ከሆኑት የመከላከያ ሠራዊት መካከል ፍሬህይወት ግርማ በሰጠችው አስተያየት እናቶችና አያቶቼ ሴትነታቸው ሳይበግራቸው ለአገር ሉዓላዊነትና ነፃነት የከፈሉትን ዋጋ ተገንዝቤ እኔም ለአገሬ ክብርና ታላቅነት ሠራዊቱን ተቀላቅያለሁ" ብላለች።


 

ይህን የአገር ክብርና ታላቅነት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ በመድገም የሠራዊቱን ህዝባዊነትና ሙያዊ ትህትና ለማረጋገጥ መዘጋጀቷንም ገልጻለች።

አገርንና ታላቁን የኢትዮጵያ ሠራዊት በመወከል ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ መታጨት በራሱ ሴቶች ያለንን ተሳትፎና ተቀባይነት እያደገ መምጣቱን ያመለክታል ያሉት ደግሞ ሌላዋ የሰላም አስከባሪ መቶ አለቃ ደጅጥኑ አያሌው ናቸው።


 

በምንሰማራበት የሰላም ማስከበር ዘመቻ አኩሪ ገድል በመፈፀም ሠራዊቱ ያለውን ተቀባይነት ይበልጥ እንዲጨምር እተጋለሁ ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለማሳካት ወደ ደቡብ ሱዳን ለመጓዝ ከሰለጠኑት መካከል 17 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸውም በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም