ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም እንዲረጋገጥ ለንግግርና ሠላማዊ አማራጮች ቅድሚያ መስጠት ይገባል -ካውንስሉ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም እንዲረጋገጥ ለንግግርና ሠላማዊ አማራጮች ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል አመለከተ።      

ካውንስሉ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የጸሎት፣ምስጋናና ምልጃ መርሃ ግብር አካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አማኞች፣ ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የተወጣጡ የኃይማኖት አባቶችና ዘማሪያን ተሳትፈዋል።

በኢትዮጵያ ሠላም፣ ዕድገትና አንድነት እንዲመጣ እንዲሁም ከፈጣሪ ጋር እርቅ እንዲወርድ በኃይማኖት አባቶች ጸሎት የተደረገ ሲሆን ህጻናትም መንፈሳዊ መዝሙሮችን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ፕሬዝዳንት ዶክተር ጣሰው ገብሬ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ መርሃ ግብሩ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ ፍቅር፣ አንድነትና ሠላም እንዲመጣ ወደ ፈጣሪ በህብረት ለመማለድ ነው።


 

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም እንዲመጣ ለሠላማዊ አማራጮችና ለንግግር ጊዜና ቦታ መስጠት እንደሚገባ በማሳሰብ ሁሉም ወገኖች ለሠላማዊ አማራጮች ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ በበኩላቸው በኢትዮጵያ አንድነትና ሠላም እንዲረጋገጥ እርስ በርስ መከባበርና የሌላውን ስሜትና ህመም መረዳት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የእምነቱ ተከታዮች የእምነቱ አስተምህሮ በሚያዘው መሰረት የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

የዘጸአት አፖስቶሊክ ሪፎርሜሽን ቤተ ክርስቲያን መሥራችና ዋና መጋቢ ሃዋሪያ ዮሃንስ ግርማ ሁላችንም ለሰላም መረጋገጥ በጋራ ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡


 

ለሰላም መስፈን ከህዝቡ ብዙ ይጠበቃል ያሉት ዋና መጋቢ ሃዋርያ ዮሃንስ ዕድገት የሚረጋገጠው ሠላም ሲረጋገጥ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

 

 

 

    

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም