የአገሪቱን የዕደ-ጥበብና የኪነ-ጥበብ ሀብቶች ተንከባክቦ ለመጠበቅ ጥረት እየተደረገ ነው

አርባ ምንጭ፤  መጋቢት 7 / 2016 (ኢዜአ)፡- የአገሪቱ የዕደ-ጥበብና የኪነ-ጥበብ ሀብቶች  ተንከባክቦና ጠብቆ  ለማሳደግ  ጥረት እየተደረገ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ። 

የፌዴራልና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የስራ ሃላፊዎች ዛሬ  በጋሞ ዞን የሚገኙ የዕደ-ጥበብና የኪነ-ጥበብ ሀብቶችን በመጎብኘት አበረታተዋል።

በዚህ ወቅት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ-ጥበብ፣የስነ-ጥበብና የፈጠራ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማሃዲ  እንዳሉት፤ የጉብኝቱ ዓላማ ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚና ገጽታ ግንባታ ያለው ድርሻ እንዲጠናከር ለመደገፍ ነው።

ሚኒስቴሩ የኪነ-ጥበብ፣የስነ-ጥበብና የፈጠራ ሥራዎችን በማስተዋወቅ፣የቴክኖሎጂ ሽግግርና የገበያ ትስስር በመፍጠሩ ረገድ አበክሮ እየሠራ መሆኑን  ተናግረዋል።

የአገራችን የኪነ-ጥበብና የስነ-ጥበብ ሀብቶች የጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ እያበረከተ ያለውን ሚና ለማጠናከር የመስሪያ ዕቃዎች እንዲዘምኑ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሠራን ይገኛል ብለዋል።

ዕደ-ጥበብና የኪነ-ጥበብ ሀብቶች ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ዘርፉን  በቴክኖሎጂ ሽግግርና በግብአት አቅርቦት ለማጠናከር ባለሀብቶች መሳተፍ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማትና ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ በበኩላቸው በጉብኝታቸው በአርባ ምንጭና ጨንቻ አካባቢ የሚገኙ የዕደ-ጥበብና የኪነ-ጥበብ እንቅስቃሴን ከተመለከቷቸው መካከል እንደሚገኙበት  ተናግረዋል።


 

በዚህም በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ተጠናክረው  ይበልጥ ተወዳዳሪ ለመሆን እንዲተጉ መነቃቃት እንዲፈጠር መደረጉን ገልጸዋል።

በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት በአገርና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እየተደረገ ያለው አበረታች ጥረት በማጠናከር ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚና ገጽታ ግንባታ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ ይሰራልም ብለዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ ድርሻ ያለው ሰፊ የዕደ-ጥበብ፣የኪነ-ጥበብና የፈጠራ ሀብቶች መኖራቸውን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወይዘሪት ፍሬህይወት ዱባለ ናቸው።


 

የዕደ-ጥበብና የኪነ-ጥበብ ኢንዱስትሪው የአገሪቱን  ብልጽግና ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ያመለከቱት ሃላፊዋ ይህን ሀብት ለመጠቀም በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ወገኖችን በማደራጀትና በመደገፍ ብሎም የገበያ ትስስር በመፍጠሩ ረገድ ቢሮው የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

የስራ ሃላፊዎቹ  በአርባ ምንጭ የጃኖ እና የሸማ ፓርኮች እንዲሁም በጨንቻ የዶርዜ መንደር  እና የማረሚያ ተቋም ዕደ-ጥበብና የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም