ቀጥታ፡

ስፖርቱን ከመንግስት ድጎማ ጥገኝነት አላቆ ራሱን እንዲችል ለማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ ነው - የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የስፖርቱን ዘርፍ ከመንግስት ድጎማ ጥገኝነት አላቆ ራሱን እንዲችል ለማድረግ ለፌዴሬሽኖችና ማህበራት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የከተማዋ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

በመዲናዋ ከሚገኙ የስፖርት ፌዴሬሽኖችና ማህበራት ውስጥ 10ሩ ራሳቸውን ከድጎማ ማላቀቅ የሚያስችሉ የመመዘኛ መስፈርቶችን የማሟላት ሂደት በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ ቢሮው ገልጿል።

ቢሮው ይህን ያለው የአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ምክር ቤት 14ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬ በአዲስ አበባ ባካሄደበት ወቅት ነው።


 

የቢሮው ኃላፊና የምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ በላይ ደጀን ባለፈው አንድ ዓመት በስፖርቱ ዘርፍ የተከናወኑ ስራዎችን አስመልክቶ ለጠቅላላ ጉባኤው ሪፖርት አቅርበዋል።

በ2015 ዓ.ም የአዲስ አበባ ስፖርት ምክር ቤት ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፥ ምክር ቤቱ ስፖርቱን ከበጀት ድጎማ ለማላቀቅ በትኩረት መስራት እንዳለበት አሳስበው ነበር።

የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊው በላይ ደጀን በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ቢሮው በመዲናዋ የሚገኙ 36 የስፖርት ፌዴሬሽኖችና ማህበራት ከመንግስት በጀት እንዲላቀቁ እየሰራ ነው።

በዚህም የተለያዩ ስፖርቶች ራሳቸውን ችለዋል የሚያስብላቸውን መመዘኛዎች እንዲያሟሉ ቢሮው ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ብስክሌት፣ ውሃ ዋና፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶና ጅምናስቲክ የስፖርት ማህበራትና ፌዴሬሽኖች መስፈርቶቹን ለማሟላት እየሰሩ ከሚገኙት መካከል ይጠቀሳሉ።

በራስ አቅም በጀት መመደብ፣ የሰው ኃይል መቅጠር፣ አደረጃጀትና ሀብት ማሰባሰብ ላይ የሚሰራ የገበያ ቡድን ማወቀር ከመመዘኛዎቹ መካከል እንደሚገኙበት ነው ኃላፊው ያነሱት።

አትሌቲክስና እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች በራሳቸው አቅም ከመንቀሳቀስ አኳያ እንደ መልካም ተሞክሮ እንደሚነሱ አመልክተዋል።

ሌሎችም የስፖርት ፌዴሬሽኖችና ማህበራት ከድጎማ በጀት እንዲላቀቁ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በ2016 በጀት ዓመት ለስፖርት ፌዴሬሽኖችና ማህበራት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡንና ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት አንጻር የ4 ሚሊዮን ብር ገደማ ብልጫ እንዳለው አንስተዋል።

ከስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ጋር በተገናኘም በመዲናዋ 1 ሺህ 236 የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን 741ዱ ባለፉት አምስት ዓመታት የተገነቡ መሆናቸውን ነው ኃላፊው የገለጹት።

በ2015 ዓ.ም 13 የመደመር ትውልድ የሕጻናት እና ወጣቶች የመጫወቻና የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች መገንባታቸውን ጠቅሰው፥ በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት እስከ አሁን 38 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንደተገነቡ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች በ19 የስፖርት ዓይነት 123 የታዳጊ ፕሮጀክቶች መከፈታቸውንም ነው ያነሱት።

ስፖርትን ባህሉ ያደረገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በመኖሪያ፣ በመማሪያና በስራ አካባቢ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ፕሮግራም ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የአካባቢ የጤና ቡድኖችን በማጠናከር ሕብረተሰቡ ጤናውን ከመጠበቅ ባሻገር የእርስ በእርስ ግንኙነቱን እንዲያዳብር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

 

በጠቅላላ ጉባኤው የአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ምክር ቤት ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉና የስፖርት አፍቃሪ ጌታ ዘሩ ለሀገር የስፖርት እድገት ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የእውቅና ሽልማት አበርክቷል።

ጠቅላላ ጉባኤው በስፖርት ማህበራት ስራ አስፈጻሚነት ከአራት ዓመት በላይ ለሰሩ 47 ሰዎች የእውቅና ሽልማት በመስጠት በክብር አሰናብቷል።

በተጨማሪም ጉባኤው ለመዲናዋ ሁለንተናዊ የስፖርት ዕድገት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ላሉ ክለቦች፣ ተቋማትና ማህበራት እውቅና ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም