ቀጥታ፡

 ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ወደ አጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ እየገባ ነው - ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2016(ኢዜአ)፦ ለብሔራዊ መግባባትና ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ ታላቅ መሠረት የሚሆነው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ወደ አጀንዳ ማሰባሰብ  ምዕራፍ እየገባ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ማሰባሰብና የሀገራዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች አሰራር ስርዓት የግብዓት ማሰባሰቢያ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፤ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ምዕራፍ ነው ብለዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክሩ መግባባት ላይ ባልተደረሰባቸው ቁልፍ ጉዳዮች መግባባት ላይ እንዲደረስ የሚያስችል በመሆኑ፥ ኢትዮጵያውያን ተወያይተው የጋራ መፍትሔ እንዲያስቀምጡ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሀገራዊ ምክክር ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ አሁን ላይ ወደ አጀንዳ ማሰባበስብ ምዕራፍ እየተገባ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ለምክክሩ ወሳኝ እና ተከታታይ የሆኑ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፤ ለዚህም በርካታ ተባባሪ አካላት መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

በአጀንዳ አሰባሰብ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው፥ ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ ላይ ሁሉም ህብረተሰብ ተሳታፊ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን መገንዘባቸውን አንስተዋል።


 

በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በህብረታቸው አማካኝነት በምክክር ሊሳተፉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በፌዴራል ደረጃ ለሚካሄዱ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎች ተወካዮችን ቀድመው እንዲያዘጋጁ ከወዲሁ ማሳወቅ እንደሚገባም ነው ሀሳባቸውን የሰነዘሩት።

ለተነሱት አስተያየቶችና ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች፥ በምክክሩ ሂደት ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል፡፡


 

የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽነር አምባዬ ኡጋቶ፥ በኮሚሽኑ የአሰራር ሂደት የሁሉም ኢትዮጵያዊ አቋም እና አጀንዳ እንደሚስተናገድ መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡

ከምክክር ሂደቱ የሚገለል አንድም አካል የለም ያሉት ኮሚሽነሩ፥ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በህግ የተሰጠውን ሃላፊነት እየተወጣ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽኑ የተሳታፊ ልየታ ባካሄደባቸው ሁሉም ወረዳዎች አካል ጉዳተኞች እንዲካተቱ መደረጋቸውን የገለጹት ደግሞ ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን ናቸው፡፡


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በሰጡት ምላሽ፥ በምክክር ሂደቱ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችን ጨምሮ ሁሉም ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ ዛሬ ባካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የአሰራር ስርዓት ውይይት ላይ የተገኙ ተሞክሮዎችን እና ሃሳቦችን በመቀመር ለሂደቱ ስኬታማነት ጥቅም ላይ እንደሚያውላቸውም አንስተዋል።

በቀጣይም ከሌሎች ባለደርሻ አካላት ጋር የተለያዩ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል፡፡

በተካሄደው የውይይት መድረክ ሚኒስትሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ከሁሉም ክልሎች የተወከሉ ባለድርሻ አካላት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮችን ጨምሮ ሌሎችም ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም