የህክምና ተመራቂ ተማሪዎች እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን በየጊዜው በማሻሻል ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ይገባቸዋል - ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የህክምና ተመራቂ ተማሪዎች እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን በየጊዜው በማሻሻል ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ይገባቸዋል - ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2016(ኢዜአ)፦ የህክምና ተመራቂ ተማሪዎች እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን በየጊዜው በማሻሻል ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ ገለፁ።
የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በተለያዩ የህክምና ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 202 የህክምና ባለሙያዎች ዛሬ በዓድዋ ድል መታሰቢያ አስመርቋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የዜጎችን ጤንነት ለመጠበቅ በበሽታ መከላከልና ለታካሚዎች የተሻለ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ ነው።
በተለይም የእናቶችንና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ በተከናወነው ስራ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።
የሀገርን እድገት ለማፋጠን ጤናማና አምራች ዜጋ ወሳኝ በመሆኑ፤ ተመራቂዎች እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን በየጊዜው በማሻሻል ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት መስጠት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሀንስ ጫላ፥ በከተማ አስተዳደሩ ለጤና አገልግሎት ተደራሽነት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
መንግሥት በዝቅትኛ የኑሮ ሁኔታ የሚገኙና ከፍለው መታከም የማይችሉ ዜጎችን ወጪ እየሸፈነ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
ደረጃቸውን የጠበቁ አዳዲስ ሆስፒታሎች እየተገነቡ ነው ያሉት ዶክተር ዮሀንስ፥ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራትም ቀዳሚ ሥራ ነው ብለዋል።
ከዚህ አኳያ የዛሬ ተመራቂ ተማሪዎች በኮሌጁ ያገኙትን እውቀት በተግባር በማሳየት ህብረተሰቡን ማገልገል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ዶክተር ኤልያስ ተዋበ ኮሌጁ የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ከማስፋት ባለፈ ብቁ የህክምና ባለሙያዎችን ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንን ሚናውን ለማስፋትም ኮሌጁን ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለማሳደግ ሂደት መጀመሩን ጠቁመዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ተመራቂዎች ዶክተር እንዳለው ሙላቴና ዶክተር ረድኤት ፀጋዬ በትምህርት ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በመተግበር ሀገርንና ህዝብን ለማገልገል ዝግጁ ነን ብለዋል።