ቀጥታ፡

የገቢ አሰባሰብን ውጤታማ ለማድረግ ለዲጂታል አሰራር ስርዓትና የታክስ ህግ ተገዥነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል-ገቢዎች ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2016(ኢዜአ)፦የገቢ አሰባሰብን ውጤታማ ለማድረግ ለዲጂታል አሰራር ስርዓትና የታክስ ህግ ተገዥነትን ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን በመተባበር ከቀድሞ የገቢዎች እና ጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮችና ሠራተኞች እንዲሁም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተውጣጡ ምሁራን ጋር ውይይት አድርገዋል።


 

የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት መስቀሌ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፥ የገቢ አሰባሰብ እየተሻሻለ ቢመጣም ሀገሪቱ ከምታመነጨው ኢኮኖሚ አንጻር አሁንም የሚሰበሰበው ገቢ አነስተኛ ነው።

ተቋማቱ  ምቹ እና ቀልጣፋ አገልግሎቶችን ለመስጠት የዲጂታል ስራዎችን እየተገበሩ መሆኑን ገልጸው፥ ይህ አሰራርም ግብር ክፋዮች ባሉበት ሆነው ክፍያ እንዲፈፅሙ እያስቻለ ነው ብለዋል።

ግብር ከፋዮችን በቅንነት፣በፍትሃዊነት፣ በታማኝነት እና በተቀላጠፈ መንገድ ለማስተናገድ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዘመናዊ የታክስ እና ጉምሩክ አስተዳደር ስርዓት መዘርጋቱን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ በዚህም የሚሰበሰበው ታክስና ቀረጥ በየጊዜው እድገት እያሳየ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ሆኖም ከአገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ መለኪያዎች አንጻር ሲታይ ገና ብዙ ስራዎችን መስራት እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።

ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካል ለገቢ አሰባሰብ ውጤታማነት የዲጂታል አሰራሩን በአገባቡ መጠቀምና ለታክስ ህግ ተገዥ መሆንን ማረጋገጥ አለበት ነው ያሉት።

የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ኮሚሽን አመራርና ሠራተኞች እንዲሁም ምሁራን ያላቸውን እውቀት በማካፈል የገቢ አሰባሰቡን ወደተሻለ ምዕራፍ ለመውሰድ ሊያግዙ እንደሚገባ ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የጠየቁት።


 

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው፥ታክስ እና ቀረጥ የሚያጭበረብሩ፣ በግብይት ወቅት ሀሰተኛ ደረሰኝ የሚጠቀሙ አካላት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ባላቸው ኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፥ ግብር ለአገር እድገት መሰረት በመሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ታክስ በአግባቡ ሊከፍል እንደሚገባ አንስተዋል።

የታከስ ህግ ተገዥነትን ለማጠናከርና የግንዛቤ ስራዎችን ለማስፋት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ነው የተናገሩት።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም