በትግራይ ክልል ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና እየተሰጠ ነው
ማይጨው፤ መጋቢት 7/2016(ኢዜአ)፦በትግራይ ክልል ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና በነፃ እየተሰጠ መሆኑ ተገለጸ።
ህክምናው የሚሰጠው በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ ከኩሓ ሆስፒታልና ሂማሊያን 'ካታራክት' ከተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው።
የ'ሂማሊያን ካታራክት' ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ተስፋይ ተክለማሪያም ለኢዜአ እንደገለጹት ተቋማቱ በዚህ ዓመት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሕክምና በቅንጅት እየሰጠ ነው።
የማይጨው ለምለም ካርል ሆስፒታል ከሁሉም ከ800 በላይ ህሙማን አገልግሎቱን ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በሚድን የዓይን ህመም ምክንያት ህዝባችን ለአይነስውርነት መዳረግ የለበትም ያሉት አስተባባሪው፣ በቀጣይም በክልሉ ሌሎች ዞኖች አገልግሎቱ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በማይጨው ለምለም ካርል ሆስፒታል የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ባለሙያ አቶ የማነ ግተት በሆስፒታሉ ህክምና የተደረገላቸው ወገኖች አስፈላጊው ክትትል እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ከታካሚዎች መካከል የ72 ዓመት አዛውንት አቶ ሕሉፍ ገብረመድህን በተደረገላቸው ነጻ የዓይን ቀዶ ሕክምና አገልግሎት የዓይን ብርሃናቸው በመመለሱ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ ደበሳይ ተካና ወይዘሮ ዘውዱ ካልአዩ ለሁለት ዓመታት ያህል የዓይን ብርሃናቸውን አጥተው ቤት ለመዋል መገደዳቸውን ተናግረዋል።
አሁን በተደረገላቸው ህክምና ግን የዓይን ብርሃናቸው በመመለሱ ካለምንም አጋዥ የግብርና ስራቸውን ለማከናወን ጉጉት እንዳደረባቸው ተናግረዋል።