ቀጥታ፡

ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከርና ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ቁርጠኛ ነች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2016(ኢዜአ)፦ ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከርና ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ቁርጠኛ መሆኗን በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ጁንግ ካንግ ገለፁ።

አምባሳደር ጁንግ ካንግ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኮሪያ ሪፐብሊክና ኢትዮጵያ ጠንካራና ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።

ሀገራቱ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1950ዎቹ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለኮሪያ ነፃነት በጀግንነት ከተዋጉበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ አንስተዋል።

ይህም ለሁለቱ ሀገራት ወዳጅነትና ትብብር ጠንካራ መሠረት መሆኑን ገልፀዋል።

ባለፉት ዓመታት ሀገራቱ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በልማት ትብብርና ባህል ልውውጥን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ግንኙነታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን አመላክተዋል።

በቀጣይም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ለማጎልበትና አጋርነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ሀገራቸው ቁርጠኛ መሆኗን ነው አምባሳደሩ ያረጋገጡት።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ ኤዥያና የፓስፊክ ሀገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ገበየሁ ጋንጋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባሻገር ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር አላቸው።


 

ሁለቱም ሀገራት አሁን ላይ ግንኙነታቸው እያደገ መምጣቱን፣ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በቴክኖሎጂ መስኮች በጋራ መሥራታቸውን ጠቅሰው፤ የልማት ትብብሩም እየተጠናከረ መምጣቱን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያና የኮሪያ ሪፐብሊክ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1963 መጀመሩን መረጃዎች ያመላክታሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም