በመዲናዋ ዘመናዊ ቦዲ ካሜራዎች ተግባራዊ መደረጉ የትራፊክ እንቅስቃሴ ቁጥጥር ግልፀኝነት የተሞላበት የማድረግ ሥራን እያገዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ዘመናዊ ቦዲ ካሜራዎች ተግባራዊ መደረጉ የትራፊክ እንቅስቃሴ ቁጥጥር ግልፀኝነት የተሞላበት የማድረግ ሥራን እያገዘ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ዘመናዊ ቦዲ ካሜራዎች ተግባራዊ መደረጉ የትራፊክ እንቅስቃሴ ቁጥጥርን ተጠያቂነትና ፍትሃዊነትን የማስፈን ሥራን እያገዘ ነው ሲል የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
ከ400 በላይ ዘመናዊ ቦዲ ካሜራዎች ለትራፊክ ፖሊሶች ተከፋፍለው ሥራ ላይ ውለዋል።
በትራፊክ እንቅስቃሴው ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቴክኖሎጂ በተደገፈ አሠራር ለመፍታት የቦዲ ካሜራዎችን ቁጥር ለመጨመር እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።
ቦዲ ካሜራ ''በሕግ አስከባሪ አካላት ደንብ ልብሶችና በሌሎችም መሳሪያዎች ላይ የሚገጠም የካሜራ ቴክኖሎጂ'' በተለይ የሕግ ማስከበር ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ ይረዳል።
ካሜራው ሕግ አስከባሪ አካላት በሥራ ላይ ባሉባቸው አካባቢዎች ያሉ እንቅስቃሴዎችን በመቅረጽ ከሕዝብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በሚገባ ለመቃኘት ያገለግላል።
በአዲስ አበባ ፖሊስ የትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ፈቃዱ ወንድምገዙ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ቦዲ ካሜራዎች ግልፀኝነት የተሞላበት አሠራር ለመፍጠር አጋዥ ናቸው።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሬዲዮ ጋር የተገናኙ ከ400 በላይ ዘመናዊ ቦዲ ካሜራዎችን ለትራፊክ ፖሊሶች በማከፋፈል የትራፊክ እንቅስቃሴውን እየተከታተለ መሆኑን ተናግረዋል።
የቦዲ ካሜራዎቹ ትራፊክ ፖሊሱ ባለበት አካባቢ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ የሚቀርጹና የተለያዩ መረጃዎችንም መዝግበው የሚያስቀምጡ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም ከትራፊክ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዙ ሥራዎች ተጠያቂነትና ፍትሃዊነትን ባረጋገጠ አግባብ እንዲከናወኑ ምቹ መደላድል መፈጠሩን ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም ለትራፊክ መጨናነቅና ተያያዥ ችግሮች መፍትሔ የሚሰጠው በሬዲዮ በሚደረግ ግንኙነት እንደነበር አስታውሰው፤ አዳዲሶቹ ቦዲ ካሜራዎች የተሽከርካሪ ሁኔታዎችን ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎችንም ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
ካሜራዎቹ በቀጥታ በማዕከል የሚመሩና ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሲሆን፤ የትራፊክ ፍሰቱን ለማስተካከልና ለትራፊክ መጨናነቅም አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችሉ መሆናቸውን አንስተዋል።
ቴክኖሎጂው በአሽከርካሪዎችና በትራፊክ ፖሊስ መካከል ለሚፈጠሩ አለመግባባቶች በተጨባጭ ማስረጃ የተደገፈ መፍትሔ በመስጠት ችግሮችን ለመፍታት ማስቻሉንም ነው የገለጹት።
ካሜራዎቹ ውጤታማ ሥራ እየተሰራባቸው ነው ያሉት ኮማንደር ፈቃዱ፤ የካሜራዎቹን ብዛት ካሉት የትራፊክ ፖሊሶች ቁጥር ጋር ለማጣጣም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የትራፊክ ዲቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ያደሳ ሚደቅሳ፤ ቴክኖሎጂው በተለይ ለትራፊክ መጨናነቅ መፍትሔ ለመስጠት ሰፊ እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ካሜራዎቹ እያንዳንዱን ክስተት የተመለከተ ማስረጃ ስለሚያቀርቡ ማኅበረሰቡ እንግልት እንዳይደርስበት የሕግ አስከባሪ አካላትም ለተለያዩ ጫናዎች እንዳይዳረጉ ይረዳል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ፖሊስ የትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ የሞተር እጀባና ቁጥጥር አባል ምክትል ኢንስፔክተር ኃይለማርያም ዘሪሁን በበኩላቸው፤ ቴክኖሎጂው መጀመሩ ዘርፉን አስተማማኝ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን ገልፀዋል።
ችግሮችን ለመለየትና ለማስተካከል ምቹ መደላድል የሚፈጥር በመሆኑ የሕግ አስከባሪ አካላትን አፈጻጸም ለማሻሻል የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።