በባህር ዳር ከተማ ስር በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎችና ዋግህምራ ዞን ከ45 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እየለማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር ከተማ ስር በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎችና ዋግህምራ ዞን ከ45 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እየለማ ነው
ባህር ዳርና ሰቆጣ ፤ መጋቢት 7/2016 (ኢዜአ)፦ በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎችና በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ከ45 ሺህ 600 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እየለማ መሆኑ ተገለፀ።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ የሆልቲካልቸር ባለሙያው አቶ ሞላለኝ መንግስቱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከተማ አስተዳደሩ ስር በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች የበጋ መስኖ እየተከናወነ ነው።
ዘንድሮም 45 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የበጋ ስንዴ፣ ሽንኩርት፣ ጎመን፣ ድንች፣ ቲማቲምና ሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ እየለማ ነው ብለዋል።
እስካሁን በመስኖ ከለማው መሬት ላይ 146 ሺህ 900 ኩንታል አትክልና ፍራፍሬ ምርት መሰብሰብ እንደተቻለም ተናግረዋል።
በከተማዋ አካባቢ የሚመረተው ምርትም የአትክልት አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማዋ ሹምአቦ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ነጋሽ ልሳነወርቅ እንዳሉት፤ በግማሽ ሄክታር መሬታቸው ካለሙት ጥቅል ጎመን 100 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ አስረድተዋል።
አሁን ላይ ምርቱ እየደረሰ በመሆኑ ፈጥኖ በመሰብሰብ ወደ ገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
አንድ ሄክታር ገደማ መሬታቸው ላይ ቀይ ሽንኩርትና ድንች በማልማት ላይ የሚገኙት ደግሞ የወራሚት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አሰበ ዳኛው ናቸው።
አሁን ላይ ወቅቱን ጠብቆ በመኮትኮት ተባይ በመከላከልና ሌሎች እንክብካቤዎችን እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው ከ160 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚያገኙም ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ እንደገለፁት በዞኑ 6 ሺህ 949 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ እየለማ ነው።
እስካሁን በተደረገው ጥረትም 578 ሄክታር መሬት በስንዴ የለማ ሲሆን ምርታማነቱን ለማሳደግም 1 ሺህ 500 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና 500 ኩንታል ምርጥ ዘር ቀርቧል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ከ28 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በሚካሄደው የመስኖ ልማት 578 ሺህ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል ነው ያሉት።