የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ አሰባሰብ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ ውይይት እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ አሰባሰብ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ ውይይት እያካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 7 /2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአጀንዳ አሰባሰብ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
በዚሁ ውይይት ማስጀመሪያ ላይ ንግግር ያደረጉት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ኮሚሽኑ መግባባት ላይ ባልተዳረሰባቸው ጉዳዮች መግባባት ላይ እንዲደረስ እየሰራ ይገኛል።
በዚህም ኢትዮጵያውያን ተወያይተው የጋራ መፍትሔ እንዲያስቀምጡ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኮሚሽኑ በወረዳዎች ደረጃ ሲያከናውን የቆየውን የተሳታፊ ልየታ ሥራዎች በተሳካ ሁኔታ ማካሄዱን ገልፀዋል።
ሀገራዊ ምክክር ለሀገረ- መንግሥት ግንባታ ታላቅ መሠረት የሚጥል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ አሁን ላይ ወደ ተግባር ምዕራፍ እየገባ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ለምክክሩ ወሳኝ እና ተከታታይ የሆኑ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፤ ለዚህም በርካታ ተባባሪ አካላት መሳተፋቸውን ተናግረዋል።
ለበርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሀገራዊ ምክክር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መሰጠታቸውንም ገልፀዋል።
በሀገራዊ የምክክር ሂደት ለትውልድ የምትመች ሀገር ለማስተላለፍ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ አሰባሰብ ሂደት ማስጀመሪያ የአሰራር ስርዓት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው ብለዋል።
እየተካሄደ በሚገኘው የውይይት መድረክ ሚኒስትሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ከሁሉም ክልሎች የተወከሉ ባለድርሻ አካላት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።