ቀጥታ፡

በክልሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ድህነትን መቀነስ የሚያስችሉ የልማትና መልካም አስተዳደር ግንባታ መሰረት ተጥሏል - አቶ አሻድሊ ሃሰን

አሶሳ ፤  መጋቢት 7/ 2016 (ኢዜአ)፡-  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት የለውጥ ዓመታት የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ በመመለስ ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የልማትና መልካም አስተዳደር ግንባታ መሰረት መጣሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከ2010 ዓ.ም ወዲህ ባሉት የለውጥ ዓመታት አገሪቷን ከድህነት በማውጣት፣ የውጭ ዕዳን በመቀነስና የበለጸገች ሀገር ገንብቶ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ የሚያስችሉ የልማትና መልካም አስተዳደር ሪፎርሞችን በመተግበር ላይ ይገኛል።

በተለይም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን በመተግበር፣ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን እና በአይሲቲ የኢኮኖሚ አውታሮች ትኩረት ተሰጥቶ እየተተገበረ ነው።

ክልሎችም ሕዝቦቻቸውን ባሳተፈ መልኩ የልማት እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ይገኛል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን እንደገለጹት፤ ክልሉ በለውጥ ዓመታት በፈተናዎች ውስጥ ሆኖ ድህነትን ለመቀነስና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሚያስችሉ የልማትና መልካም አስተዳደር ግንባታ ስራዎች መሰረት ተጥሏል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ በሀገራዊ የለውጥ ዓመታት የክልሉ ህብረተሰብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችን ለመመለስ ያላሰለሰ ጥረት መደረጉን ጠቁመው፤ በማህበረሰባዊ ዘርፎች የተገኙ ውጤቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል።  

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከ161 በላይ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ እንደሚገኙ ያነሱት አቶ አሻድሊ፤ ከለውጡ ወዲህ ባሉ ዓመታት የተከናወኑ የልማት ስራዎች የላቀ ስኬቶች ለመገኘታቸው ማሳያ ናቸው ይላሉ።

ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለማስፋፋትና አገልግሎታቸውን ለማሻሻል በተደረገ ርብርብ የተገኙ ውጤቶችን አንስተው፤ ይህም በክልሉ በየደረጃው የተማረ የሰው ሃይልን ለማብዛት አስችሏል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡

ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በማልማት ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ጥረት መደረጉን አመልክተው፤ በተለይም ሰፋፊ ለም መሬትን ለማልማት እና ማዕድናትን አውጥቶ ለመጠቀም የተደረገውን ጥረት እንደ ማሳያ ጠቅሰዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በኢንቨስትመንት ስም ሰፊ የእርሻ መሬት እጃችን አልነበረም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የእርሻ መሬቱን በማስመለስና በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች በማስተላለፍ በሚገባ ማልማት መቻሉን አብራርተዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ አነስተኛ የመስኖ ግድቦች እንደተገነቡ ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛዎችን በማስፋፋትና በሌሎች ግብዓት የሰብል እና የእንስሳት ምርታማነትን በመጨመር ረገድ የተደረገውን እንቅስቃሴ አንስተዋል፡፡

መስኖን በስፋት በመጠቀም በዓመት ሁለት ጊዜ በማልማት የምግብ ዋስትናቸውን ያረጋገጡ ቤተሰቦች ቁጥር መጨመሩን አቶ አሻድሊ ጠቁመው፤ ለገበያ በማቅረብ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት የቻሉትንም አንስተዋል፡፡

የክልሉ መንግስትም የረጅም እና የአጭር ጊዜ ስትራቴጂ እቅድ በማውጣት ከፍተኛ በጀት፣ ሎጂስቲክስ እና የሰው ሃይል በመመደብ ዘላቂ የመልሶ ማቋቋም ስራ እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም