ቀጥታ፡

ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ የአካባቢ ሥነ-ምህዳር ጥበቃ ሥራ ለማስፋት እየተሰራ ነው - ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2016 (ኢዜአ)፦ ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ የአካባቢ ሥነ-ምህዳር ጥበቃ ሥራ በማስፋት ብዝኃ ሕይወትን በዘላቂነት ለመጠበቅና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

32ኛው የኢትዮጵያ ሥነ-ሕይወት ባለሙያዎች ማኅበር ጉባኤ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ መንግሥት የግብርና ምርታማነትን ማስቀጠል የሚያስችሉ አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረገ ነው።

በሥነ-ምኅዳር ጥበቃና በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የተከናወኑ ተግባራትም የተራቆተ የመሬት ገጽታን በመመለስ ምርታማነት እንዲጨምር እያደረጉ ነው ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሩ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ለሥነ-ምኅዳር ጥበቃ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ሥነ-ሕይወት ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ቢቂላ ወርቅነህ፤ በጉባኤው የሥነ-ምኅዳር ጥበቃ ላይ ያተኮሩ የምርምር ሥራዎች ቀርበው ምክክር እንደተደረገባቸው ገልጸዋል።

የምርምር ውጤቶችም ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለአስፈፃሚ አካላትና ለምርምር ተቋማት በግብዓትነት እንዲያገለግሉ ይደረጋል ብለዋል።

የምርምር ሥራዎቹም የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የተራቆቱ አካባቢዎችን እንዲያገግሙ በማድረግ የመጣውን ውጤት የሚያስቀጥሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ሥነ-ሕይወት ባለሙያዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ቤዛወርቅ አፈወርቅ፤ በኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች የደን ሽፋን እንዲጨምር አስችሏል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተመዘገበውን ውጤታማ ደን ልማት ለማስቀጠል በጥናትና ምርምር የታገዙ ሥራዎችን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል።


 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ሁነኛ መፍትሔ ነው ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ተመራማሪ ዶክተር ገመዶ ዳሌ ናቸው።

በአረንጋዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተመዘገበ የመጣውን ውጤት ለማስቀጠል የዘርፉ ተመራማሪዎች አዎንታዊ ሚናቸውን መጫወት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

32ኛው የኢትዮጵያ ሥነ-ሕይወት ባለሙያዎች ማኅበር ጉባኤ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ተካታታይ ቀናት እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም