ልዩ ልዩ ቅርሶች ያሏቸው ግለሰቦች ቅርሶቹን ለኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም እንዲለግሱ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ልዩ ልዩ ቅርሶች ያሏቸው ግለሰቦች ቅርሶቹን ለኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም እንዲለግሱ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ለታሪክ ግብዓትነት የሚውል ቅርሶች ያሏቸው ግለሰቦች ቅርሶቹን ለተቋሙ እንዲለግሱ ጥሪ አቀረበ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ለምርምር ግብዓትና ለተለያዩ ፋይዳ ያላቸው ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ለታሪክ ምርምርና ለዕይታ የሚውሉ ልዩ ልዩ ቅርሶችና ሥጦታዎችን ዛሬ ተረክቧል።
ተቋሙ የተረከባቸው ከተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ግለሰቦች የተበረከቱ የመካከለኛው ዘመን መገበያያ ሳንቲሞች፣የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ፎቶዎችና ዶክመንቶች፣ መጻሕፍትና ሌሎች ታሪካዊ ቁሳቁሶች ናቸው።
የርክክብ ሥነ-ሥርዓት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታከለ መርዕድ፣ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ወዳጆች ማኅበር አባላት፣ የሥጦታ አስረካቢ ግለሰቦችና ተወካዮችና ምሁራን በተገኙበት ዛሬ ተከናውኗል።
ከሥጦታዎች መካከልም በ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ዓመታት በኖሩ ጀርመናዊያን ፎቶ አንሺዎች የተነሱና የዘመኑን ሁለንተናዊ መልኮች የሚገልፁ ምስሎችን ያካተቱ ሦስት የፎቶ አልበሞች እንዲሁም በእንግሊዛዊው ፕሮፌሰር ኒል ሙኒሮ የተበረከተው በ1973 የተነሳ ፊልም ይገኝበታል።
በዶክተር ሁሴን ሰይድና አቶ ወንድማገኘሁ ግዛው የተሰባሰቡ 22 የመካከለኛው ዘመን ሳንቲሞች፣ የዕውቁ ጋዜጠኛ ጌታቸው ተድላ 65 ፎቶግራፍ ስብስቦች፣ የአፄ ኃይለሥላሴ ፓስፖርትና ሰነዶች እንዲሁም ከ300 በላይ መፃሕፍት ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ታከለ መርዕድ (ዶ/ር)ን ለኢዜአ እንደተናገሩት ምርምር ተቋሙ የተረከባቸው ሥጦታዎች ለተቋሙ ተልዕኮ ስኬት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው።
ለታሪክ ተመራማሪዎችም ትልቅ ግብዓት እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ወዳጆች ማኅበር ኮሚቴ አባል ዶክተር አሉላ ፓንክረስት፤ በዕለቱ የተበረከቱ ፎቶግራፎች፣ ሳንቲሞችና ሰነዶች ለጥናትና ምርምር ትልቅ ግብዓት እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
ከጣሊያ ወረራ በፊት የነበሩ ታሪኮችን የሚገልጹ ፎቶግራፎች የዘመኑን ታሪክ ለመመራመር ይጠቅማሉ ብለዋል።
በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተመረቱ ከግብፅ የመጡ ሳንቲሞች ለኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ታሪክ ጥናት ትልቅ አበርክቶ ይኖራቸዋል ነው ያሉት።
ምሁራኑ ለአገራዊ ጥናትን ምርምር የሚበጁ ቅርሶችና ሰነዶች በተለያዩ ግለሰቦች እንደሚገኙ ገልጸው፤ መሰል የመረጃ ሃብቶች በተቋሙ ቢበረከቱ ለአገር ታሪክ ጥናትና ለቅርሶች መጠበቅ ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረክታሉ ብለዋል።
በዚህም ለአገር ታሪክ ጥናት የሚበጁ ቅርሶችን የያዙ ግለሰቦችም በውርስም ሆነ በሌላ መንገድ የያዟቸውን ታሪካዊ ቅርሶችና ሰነድ ስብስቦች ለጥናትና ምርምር ተቋሙ እንዲያስረክቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ተቋሙ ከተረከባቸው መከከል በጀርመናዊያን ፎቶ አንሺዎች የተነሱ በሶስት አልበም የታቀፉ 1 ሺህ 500 ገደማ ፎቶግራፎችን ያስረከቡት በኢትዮጵያ ሃይማኖት ታሪኮች ተመራማሪው ዶክተር ዩርገን ክላይን ናቸው።
ፎቶግራፎቹ ከመፅሀፍት የማይገኙ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ታሪኮችና እሴቶችን የሚያስነብቡ በመሆናቸው ለኢትዮጵያ ታሪክና አሴት ይበልጥ ለማጥናት አይተኬ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
በሌሎች አገራት የሚገኙ ኦርጂናል ፎቶግራፎች ለተቋሙ ቢሰጡ ለኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት ትልቅ ዕድል እንደሆነም ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ በፈረንጆቹ 1973 የተቀረጸ የኢትዮጵያን መልክዓ ምድር የሚያስቃኝ የአየር ላይ ፊልምን ያስረከቡት የአፈር ሳይንስ ባለሙያና መዛግብት ማሰባሰብ ላይ የሚሰሩት እንግሊዛዊ ፕሮፌሰር ኒል ሙኑሮ ናቸው።
ፕሮፌሰሩ በወቅቱ የተቀረጸው ፊልም በትግራይ አካባቢ ለነበረ የገጠር ልማት ጥናት ዓላማ ፊልሙን መሰብሰባቸውን አስታውሰዋል።
በጥናቱ የአየር ላይ ፊልሞችን ጨመሮ የተለያዩ የመረጃ መንጮች እንደነበሩ አስታውሰው፣ ዛሬ ላይ እነዚህ የመረጃ ሃብቶችን ወደ ትክክለኛው ሥፍራ እንዲቀመጡ ፍላጎት ስላላቸው ለማስረከብ መወሰናቸውን ገልጸዋል።
በዘመኑ ቴክኖሎጂ የተቀረጹ ፊልሞች ዲጂታላይዝ በማድረግ ለታሪክ ግብዓት መጠቀም እንደሚያስችልም ተናግረዋል።