የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመስክ ምልከታ እያደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመስክ ምልከታ እያደረጉ ነው

ቦንጋ/ ሶዶ/ ሐረር ፤ መጋቢት 6 /2016 (ኢዜአ)፡- የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋን ጨምሮ ሌሎችም የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመስክ ምልከታ እያደረጉ ነው።
በደቡብ ኢትዮጵያና በሐረሪ ክልሎችም ተመሳሳይ መረሃ ግብር ተዘጋጅቷል።
ዶክተር ፍጹም አሰፋ እንደገለጹት፤ ምልከታዉ በክልሉ፣ በዞንና እና ከተማ አስተዳደር የተሰሩ ስራዎች ያካትታል።
ተግባራቱ ያሉባትን ደረጃ በመገምገም የገጠማቸውን ጠንካራና ደካማ ጎኖች መለየት የምልከታው ዓላማ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም በአፈጻጸም ሂደት ላጋጠሙ ችግሮች በጋራ መፍትሔ የሚፈለግበት መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ በቀጣይ ተሞክሮን በመቅሰም ተግባራትን ለማጠናከር የሱፐርቪዥን ቡድኑ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግሥት በክልሉ የሚያካሂደው ተከታታይ ምልከታና ድጋፋዊ ሱፐርቪዥን በክልሉ የሚከናወኑ ተግባራት የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖራቸው እንደሚያግዝ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ናቸው።
ለተመሳሳይ መረሃ ግብር የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለምና ሌሎች የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በወላይታ ሶዶ ከተማ ተገኝተዋል።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፤ መረሃ ግብሩ በክልሉ በተያዘው የበጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራት ጠንካራና ደካማ ጎኖች መለየትን ዓላማ ያደረገ ነው።
ይህም ጠንካራ ጎኖችን በማጎልበትና ድክመቶችን በማረም የድጋፍና ክትትል ለማድረግ ብሎም የክልሉን አቅም ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል።
ከነገ ጀምሮ በክልሉ ዞኖች፣ ወረዳና ቀበሌዎች ላይ የመስክ ምልከታ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ፤ ግምገማና የመስክ ምልከታው በተለይ ክልሉ አዲስ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የውስጥ አቅምን ከመገንባት አኳያ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚልና ሌሎች የፌደራል መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሐረሪ ክልል በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ይጎበኛሉ።
የከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ሐረር ከተማ ሲደርሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ከሌሎች የአመራር አባላት ጋር በመሆን አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በክልሉ በሚያደርጉት ቆይታ የክረምት የአረንጓዴ አሻራና የበጎ አድራጎት ስራዎች፣ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርና ሌሎችንም ተግባራት የመስክ ምልከታ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።