ቀጥታ፡

ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ ለማድረስ ሴቶችን ማብቃትና ተሳትፏቸውን ማሳደግ ይገባል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2016(ኢዜአ)፦ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ ለማድረስ ሴቶችን ማብቃት፣ ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለጸ።

የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓለም ለ113ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ መከበሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም በዓሉን "ሴቶችን እናብቃ ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ" በሚል መሪ ኃሳብ የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች በተገኙበት በዛሬው ዕለት አክብሯል።

ይህንንም ተከትሎ ከሴትነት ጋር በተያያዘ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚስተዋሉ የተዛቡ አመለካከቶችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ያተኮረ ውይይት ተደርጓል።


 

የጋብቻና የቤተሰብ አማካሪ ይመስገን ሞላ በዚሁ ጊዜ፤ በሀገሪቱ በሴቶች ላይ የሚነሱ የተለያዩ የተዛቡ አመለካከቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በማኅበረሰቡ ዘንድ የሴቶችን አቅም አሳንሶ ማየትና ሴት ልጅ የራሷ ዓላማና ግብ አላት ብሎ ከማሰብ አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን አንስተዋል።

ይህም በሀገሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የራሱ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው ተናግረዋል።

በመሆኑም ይህ አመለካከት መቀየር እንዳለበት ገልጸው ሴቶች በማንኛውም የሥራ መስክ ተሰማርተው ውጤታማ የመሆን አቅም አላቸው ብለዋል።

ይህን አቅማቸውን ወደ ፊት ማውጣት እንደሚገባቸውም ነው የገለጹት።

ይህንንም እውን ለማድረግ በተለይም የሚመለከታቸው አካላት ሴቶችን ከማብቃት ረገድ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሴቶችና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክተር ታደለች ቦጋለ ተቋሙ የሴቶችን አቅም ለማጎልበት የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ነው መሆኑን ገልጸዋል።

ሴቶች በሚሰሩበት ሙያ ወደ ፊት እንዲመጡ ለማስቻልም ሌሎች የአቅም ግንባታ ድጋፎች እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም