በኢትዮጵያ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ሆነዋል - ብሔራዊ የመታወቂያ ፕሮግራም - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ሆነዋል - ብሔራዊ የመታወቂያ ፕሮግራም
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት መሆናቸውን ብሔራዊ የመታወቂያ ፕሮግራም አስታወቀ።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ መስሪያ ቤቶች በፕሮጀክት ደረጃ ሲተገበር ቆይቷል።
የፕሮግራሙን ተቋማዊ አሰራርና ውጤታማነት ለማሳደግ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅ 1284/2015 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አቤነዘር ፈለቀ በፕሮግራሙ አማካኝነት 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ማግኘታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በፕሮግራሙ የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ለሚያሟሉ ነዋሪዎች ባለ 12 አሃዝ ልዩ የፋይዳ መለያ ቁጥር እንደሚሰጥና ይህ መለያ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ተደርገው እንደሚቆጠሩ አመልክተዋል።
በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ዜጎችን ቁጥር ወደ 10 ሚሊዮን ለማድረስ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ዜጎች መታወቂያውን እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር አገልግሎቱን ከተለያዩ ተቋማት ጋር የማስተሳሰር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት እንዲሁም የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ከዲጂታል መታወቂያ ጋር የተገናኘ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቅርቡም ኢትዮጵያ ለስደተኞች የዲጂታል መታወቂያ መስጠት መጀመሯን አስታውሰው በባንኮች የፋይናንስ ግብይትና መሰል አገልግሎቶችን በመታወቂያው የመስጠት ስራ ለማስፋት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ትምህርት፣ ጤናና ማህበራዊ ዋስትና በቀጣይ አገልግሎቱ የሚተገበርባቸው መስኮች መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት።
የዲጂታል መታወቂያ ከተቋማት ጋር መተሳሰሩ የአገልግሎቱን ተጠቃሚ ቁጥር ለማሳደግ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።
አቶ አቤነዘር ከዲጂታል መታወቂያ ጋር በተያያዘ በአንዳንዶች ዘንድ ብዥታዎች መኖራቸውን ጠቅሰው የዲጂታል መታወቂያው የተዘጋጀው የቀበሌ መታወቂያን ለመተካት አለመሆኑን ገልጸዋል።
መታወቂያው የሚሰጠው አገልግሎት የቀበሌ መታወቂያን የሚመግብ እንጂ የሚተካ አይደለም ብለዋል።
የዲጂታል መታወቂያ በኢትዮጵያ የሚኖር ማንኛውም ዜጋ የራሱን ማንነት የሚገልጽበት መለያ መሆኑን ተናግረዋል።
የዲጂታል መታወቂያ ማውጣት አስገዳጅ ሊደረግ ነው የሚለው መረጃ ትክክል እንዳልሆነም ነው አቶ አቤነዘር የገለጹት።
የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ላይ ዜጎች መታወቂያውን የሚያወጡት በፈቃደኝነት ላይ ተመስረተው እንደሆነ በግልጽ እንደሚያስቀምጥ ጠቅሰው ተቋሙ ዜጎች መታወቂያውን በአስገዳጅነት እንዲያወጡ ማድረግ እንደማይችል ተናግረዋል።
ይሁንና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለደንበኞቻቸው ለሚሰጡት አገልግሎት ዲጂታል መታወቂያን መጠቀምን እንደ ግዴታ ማስቀመጥ ይችላሉ ብለዋል።
በዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ወቅት ከዜጎች የሚወሰዱ መረጃዎች ለሶስተኛ ወገን ተላልፈው እንደማይሰጡና ለዚህም የግል መረጃን መጠበቅ የሚያስችል የአሰራር ማዕቀፍ እንዳለ አንስተዋል።
የዲጂታል መታወቂያ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል አካታች በማድረግ ማንነታቸውን የሚገልጽ ማስረጃ እንዲይዙ ማድረግ የሚያስችል አማራጭ መሆኑን ዳይሬክተሩ አክለዋል።
በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት 90 ሚሊዮን ዜጎችን የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ መታቃዱም ተገልጿል።