ቀጥታ፡

የጤና ተቋማት በአክሪዲቴሽን ሥርዓት ውስጥ እንዲያልፉ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2016(ኢዜአ)፦የአገሪቱን የጤና አገልግሎት ውጤታማ ለማድረግ የጤና ተቋማት በአክሪዲቴሽን ሥርዓት ውስጥ እንዲያልፉ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።  

በጤና ሚኒስቴር የጤና ሥርዓት ኢኖቬሽንና ጥራት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አባስ ሐሰን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የጤና አገልግሎቱን ጥራትና ተደራሽነት ለማሳደግ በርካታ የሪፎርም ተግባራት እየተከናወኑ ነው።  

ጤና ተቋማት በግብዓት፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በመሰረተ ልማትና መረጃ አያያዝ ያላቸውን ደረጃ ማሳደግ ለጤና አገልግሎት ጥራት ቁልፍ ከሚባሉ ጉዳዮች መካከል መሆናቸውን አብራርተዋል።

የጤና ተቋማት በአክሪዲቴሽን /እውቅና/ ሥርዓት ውስጥ እንዲያልፉ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎትና የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢኒስቲትዩት በጋራ ለመሥራት ሥምምነት መፈራረማቸውን ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር አባስ ገለጻ፤ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ምን ዓይነት መስፈርቶችን ማሟላት አለባቸው?፣ አስፈላጊው ግብዓት አሟልተዋል ወይ?፣ በቂ መሰረተ ልማት ይዘዋል ወይ? የሚሉ ጉዳዮች ተመዝኖ እውቅና የሚሰጥበት ሥርዓት የሚዘረጋም ይሆናል። 

መሪ ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት፤ የአስር ዓመት ፍኖተ ካርታ የተዘጋጀ ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ የጤና ተቋማት እውቅና አሰጣጥ ሥርዓት ይዘረጋል።  

የጤና ተቋማትን አክሪዴቴሽን ሥርዓት ውስጥ ለማስገባት የሚደረገው ዝግጅት በዚህ ዓመት የሚጠናቀቅ ሲሆን ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ አሰራሩ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

የጤና ተቋማት የአክሪዲቴሽን ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉ የሕክምና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል የሚኖረው ፋይዳ የላቀ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

የጤና አገልግሎት በጥራት፣ በፍትኃዊነትና ፈጠራ በታከለበት መልኩ ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ከተያዙ ግቦች መካከል የአመራርን ብቃትና ውጤታማነት ማሳደግ ተጠቃሽ ነው።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ የውጤታማ አመራር መርኃ ግብር መቀረጹን ገልጸው መርኃ ግብሩን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል ሲሉም አብራርተዋል።

 

 

     

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም