ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን በአገሪቱ ሰላምን ለማፅናት ሴቶች የሚጠበቅባቸውን ሚና  እንዲወጡ  እየደገፈ  ነው

አዳማ፤ መጋቢት 6/2016(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን በአገሪቱ ሰላምን ለማፅናት ሴቶች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ እየደገፈ   መሆኑን  የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ገለጸ።

ፌዴሬሽኑ ከሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ የፌዴሬሽኑ አመራር አባላት የአመራር ሰጪነት ሚና ላይ ያተኮረ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናና የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ  መድረክ በአዳማ ከተማ እያካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አስካለ ለማ እንደገለጹት፤ ፌዴሬሽኑ በአገሪቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው  እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሴቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ይደግፋል።

መድረኩ የተዘጋጀውም በተለይ ሴቶች በሰላም ግንባታ  ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ የየክልሎቹ የፌዴሬሽን አመራር አባላት  የማስፈጸም አቅማቸውን ለማጎልበት  እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህም በቂ የማስፈፀም ክህሎትና አቅም እንዲገነቡ ያለመ ግምገማ እንደሚካሄድ ያመለከቱት ወይዘሮ አስካለ ፤ በቀጣይ በአገር ሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ላይ በየደረጃው የሚገኙ የሴቶች አደረጃጀቶች ከመንግሥት ጋር ተቀናጅተው በትብብር እንዲሰሩ ለማስቻልም ነው ብለዋል።

እንዲሁም  ሴቶች መልካም አስተደደር እንዲረጋገጥና የሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲጠናከር በአቅም  ማብቃት ላይም  እየደገፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይ በየደረጃው ባለው መንግስታዊ መዋቅር ላይ ያሉ ሴቶች ፈጠራና ፍጥነት የታከለበት ሳይንሳዊ የአመራር ሰጪነት ሚና እንዲወጡም እንዲሁ።


 

የኦሮሚያ ክልል ሴቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ፀገነት ሃይሌ በበኩላቸው ፤መድረኩ  የሴቶች የማስፈፀም አቅም የሚያጎለብት በተለይ በስራ ሂደት ውስጥ  እያጋጠሙን ያለው  የአመራር ሰጪነት ክፍተት  የምንቀርፍበት ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የሴቶች አደረጃጀቶች በአገር ሰላምና ፀጥታ ማስፈን ረገድ የጎላ ሚና እንዲጫወቱ የሚያግዝ  መሆኑን ገልጸዋል።

የሃዳ ሲንቄ የሰላም ማህበር በማደራጀት በክልሉ የሚስተዋሉ የሰላምና ፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው ፤ በተለይ የሴቶች አደረጃጀቶች ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር  ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ኢፍቱ አባስ ፤ በአስተዳደሩ ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሴቶች  ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ተናግረዋል።

በአለመግባባት በሚፈጠር ችግር የመጀመሪያው ተጎጂዎች ሴቶችና ህፃናት  መሆናቸውን አውስተው፤  "ቡና ለሰላም " በሚል ሀሳብ  ሰላም የዕለት አጀንዳቸው እንዲያደርጉ ማመቻቸታቸውን ገልጸዋል።

ሰላም ልጆች ትምህርት ቤት መላክና ሰርቶ ለመለውጥ  ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን አጀንዳ አድርገው በጎረቤት፣ በአካባቢና በቀበሌ  ሰላም እንዲጠበቅ በትኩረት እየሰሩ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናውና የግምገማው  መድረኩ ለአራት ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም